በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አንጄይ ኦኒስጁክ ያለፍርድ በእስር የሚቆይበትን ጊዜ በተመለከተ ውሳኔ በተደረገበት ወቅት፣ በፍርድ ቤቱ የእስረኞች ማቆያ ክፍል ውስጥ ሆኖ

ነሐሴ 9, 2019
ሩሲያ

ወንድም አንጄይ ኦኒስጁክ ብቻውን ከታሰረ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው

ወንድም አንጄይ ኦኒስጁክ ብቻውን ከታሰረ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው

የፖላንድ ዜግነት ያለው ወንድም አንጄይ ኦኒስጁክ ጥቅምት 9, 2018 ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ካዋሉት ጊዜ አንስቶ ያለፍርድ በእስር ቤት ቆይቷል። የእስር ቆይታው እንዲራዘም ሲደረግ አሁን አምስተኛ ጊዜው ሲሆን እስከ ጥቅምት 2 ድረስ በእስር እንዲቆይ ተወስኖበታል፤ ስለዚህ ያለፍርድ የሚታሰርበት ጊዜ የሚያበቃው ከታሰረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ነው ማለት ነው።

አንጄይ ከመታሰሩ በፊት ከባለቤቱ ከአና ጋር። አና፣ አንጄይ ከታሰረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት አሥር ወራት እንድትጠይቀው አልተፈቀደላትም

አንጄይ በቁጥጥር ሥር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ የታሰረው ብቻውን ነው። ከጠዋቱ 12 ሰዓት አንስቶ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ እንዲተኛ አይፈቀድለትም። በሙቅ ውኃ ገላውን እንዲታጠብ የሚፈቀድለት በሳምንት አንዴ ለ15 ደቂቃ ያህል ብቻ ነው። የአንጄይ ሚስት አና፣ አንጄይ በእስር በቆየባቸው አሥር ወራት በሙሉ እንድትጠይቀው አልተፈቀደላትም። ከአንጄይ ጋር የሚገናኙት በደብዳቤ አማካኝነት ብቻ ነው። አንጄይን ለመጎብኘት እንዲፈቀድላት በተደጋጋሚ ጥያቄ ብታቀርብም ጥያቄዋ አንዴም ተቀባይነት አላገኘም።

ከዚህ በፊት በወጣ ሌላ ዜና ላይ እንደተገለጸው አንጄይ የታሰረው የአካባቢው ፖሊሶችና ፊታቸውን የሸፈኑ ወታደሮች የእሱንና በኪሮቭ የሚኖሩ ሌሎች 18 የይሖዋ ምሥክሮችን ቤት በወረሩበት ጊዜ ነበር። አንጄይ ሃይማኖታዊ መዝሙሮች በመዘመሩና ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን በማጥናቱ ምክንያት ክስ ተመሥርቶበታል።

በኪሮቭ የሚኖሩ ሌሎች አራት ወንድሞችም (የ44 ዓመቱ ማክሲም ኻልቱሪን፣ የ66 ዓመቱ ቭላዲሚር ኮሮቤኒኮቭ፣ የ26 ዓመቱ አንድሬ ሱቮርኮቭ እና የ41 ዓመቱ ኤቭጌኒ ሱቮርኮቭ) ልክ እንደ አንጄይ ባለፈው ዓመት ያለፍርድ ታስረው ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ በቁም እስር ላይ ይገኛሉ። አንጄይ እና እነዚህ አራት ወንድሞች ጉዳያቸው በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እስኪታይላቸው እየጠበቁ ነው።

በዚህ ዓመት የሩሲያ ባለሥልጣናት በኪሮቭ በሚኖሩ ሌሎች ሰባት ወንድሞች ላይ ክስ መሥርተዋል፤ ከእነዚህ ወንድሞች መካከል በዕድሜ ትልቁ ወንድም ዬቭጌኒ ኡድንሴፍ ሲሆኑ ዕድሜያቸው 70 ዓመት ነው። በአሁኑ ወቅት በእምነታቸው ምክንያት የወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው በኪሮቭ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 12 ደርሷል።

ከአንጄይ፣ ከአና እና በሩሲያ ከሚኖሩ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር በተያያዘ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ አንዘነጋም፦ “በእስር ላይ ያሉትን ከእነሱ ጋር ታስራችሁ እንዳላችሁ አድርጋችሁ በማሰብ ሁልጊዜ አስታውሷቸው፤ እናንተም ራሳችሁ ገና በሥጋ ያላችሁ በመሆናችሁ እንግልት እየደረሰባቸው ያሉትን አስቡ።”—ዕብራውያን 13:3