በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኮንስታንቲን ሞይሰዬንኮ ከባለቤቱ ከማርጋሪታ ጋር

ሐምሌ 7, 2021
ሩሲያ

ወንድም ኮንስታንቲን ሞይሰዬንኮ የሌሎች መልካም ምሳሌነት ብርታት ሰጥቶታል

ወንድም ኮንስታንቲን ሞይሰዬንኮ የሌሎች መልካም ምሳሌነት ብርታት ሰጥቶታል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ አደረገ

መስከረም 9, 2021 የአሙር ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ኮንስታንቲን ሞይሰዬንኮ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ቀደም ሲል የተላለፈበት ፍርድ በዚያው ይጸናል። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርድም።

ሐምሌ 14, 2021 በአሙር ክልል የሚገኘው የዘይስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ኮንስታንቲን ሞይሰዬንኮ ጥፋተኛ ነው በማለት የስድስት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት ፈርዶበታል። እርግጥ ወንድም ኮንስታንቲን አሁን ወህኒ አይወርድም።

አጭር መግለጫ

ኮንስታንቲን ሞይሰዬንኮ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1976 (አባካን፣ የካካሲያ ሪፑብሊክ)

  • ግለ ታሪክ፦ መንታ የሆኑ ታናናሽ ወንድሞች አሉት። በወጣትነቱ ማርሻል አርትስ ይሠራ ነበር። የኮምፒውተር ሲስተም ባለሙያ እና መሐንዲስ ሆነ

    የፋሽን ዲዛይነር ከሆነችው ከማርጋሪታ ጋር በ1998 ትዳር መሠረተ። በ2000 መጀመሪያ አካባቢ ሁለቱም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመሩ። ኮንስታንቲን መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክና ከሳይንስ አንጻር ትክክል መሆኑን ሲገነዘብ ይበልጥ ለመማር ተነሳሳ። እሱና ባለቤቱ በዚያው ዓመት ተጠመቁ

    አባቱ የሞተው ከአሥር ዓመት በፊት ነው። ኮንስታንቲን ዓይነ ስውር የሆኑትን አያቱን ለስድስት ዓመታት ተንከባክቧል፤ አያቱ በቅርቡ ሕይወታቸው አልፏል

የክሱ ሂደት

በአሙር ክልል የሚገኘው የፌዴራል ደህንነት አገልግሎት የወንጀል ምርመራ ዲፓርትመንት መጋቢት 11, 2019 በወንድም ኮንስታንቲን ሞይሰዬንኮ ላይ ክስ መሠረተ። በኋላም ፖሊሶች ኮንስታንቲንን ጨምሮ የአምስት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በረበሩ። ፖሊሶቹ ላፕቶፖችን፣ የሞባይል ስልኮችን እና የግል ሰነዶችን ወረሱ። ኮንስታንቲን በሩሲያ ፌዴሬሽን የጽንፈኞች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል፤ በዚህም የተነሳ የባንክ ሒሳቡን ማንቀሳቀስ አይችልም።

ኮንስታንቲን እሱና ባለቤቱ በ2018 በሶል፣ ደቡብ ኮሪያ በተካሄደው የክልል ስብሰባ ላይ መገኘታቸው በጣም እንዳበረታታቸው ገልጿል። በስብሰባው ላይ አንዱ ተናጋሪ በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ታስረው የሚያውቁ ተሰብሳቢዎች በሙሉ ከተቀመጡበት እንዲነሱ ጠየቀ። ኮንስታንቲን እንዲህ ብሏል፦ “በስታዲየሙ ውስጥ የነበሩት ወንድሞች በሙሉ ማለት ይቻላል ተነሱ። ከዚያም [ተናጋሪው] ‘አያችሁ! በሰላምና በደህና እየኖሩ ነው!’ አለ። ይህም ፈተናን በጽናት መቋቋም እንደሚቻል በግልጽ አሳይቶኛል።” ተናጋሪው “በጠላቶቼ ፊት ማዕድ አዘጋጀህልኝ። ራሴን በዘይት ቀባህ፤ ጽዋዬ ጢም ብሎ ሞልቷል” የሚለውን መዝሙር 23:5⁠ንም ጠቅሶ ነበር። ኮንስታንቲን ይህ ጥቅስ ልቡን እንደነካው ተናግሯል።

ኮንስታንቲን የወንድማማች ማኅበሩ የሚሰጠውን ድጋፍም ከፍ አድርጎ ይመለከታል። በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በእሱ ላይ የተመሠረተውን ክስ በትኩረት እንደሚከታተሉና በጸሎታቸው እንደሚያስቡት ማወቁ በጣም ያስገርመዋል። እንዲህ ብሏል፦ “በአገራችን ውስጥ ስደት ከሚደርስበት ከእያንዳንዱ ወንድም ወይም እህት ጎን እጅግ ብዙ የእምነት ባልንጀሮቻቸው እንደተሰለፉ ይሰማኛል። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ሕይወታችንን ለወንድሞቻችን አሳልፈን የመስጠት ግዴታ አለብን’ የሚለውን 1 ዮሐንስ 3:16⁠ን ተግባራዊ እያደረጉ ነው።”

ይሖዋ በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እያጠነከራቸው እንዳለ ስንሰማ በጣም ደስ ይለናል። እኛም ስደት ሲደርስብን “ብርታትና ኃይል” እንደሚሰጠን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።—መዝሙር 68:35