በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኮንስታንቲን ባዠኖቭ በሩሲያ ከሚገኝ እስር ቤት ከተለቀቀ ከ14 ቀን በኋላ ማለትም ግንቦት 19, 2021 ድንበሩን አቋርጦ ዩክሬን እንደገባ ከባለቤቱ ጋር ሲገናኝ

ግንቦት 20, 2021
ሩሲያ

ወንድም ኮንስታንቲን ባዠኖቭ ከሩሲያ ከተባረረ በኋላ በሰላም ዩክሬን ደርሷል

ወንድም ኮንስታንቲን ባዠኖቭ ከሩሲያ ከተባረረ በኋላ በሰላም ዩክሬን ደርሷል

ግንቦት 5, 2021 ወንድም ኮንስታንቲን ባዠኖቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተለቀቀ። a ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ የተወሰኑ ቀናት ያህል ካሳለፈ በኋላ ግንቦት 19, 2021 ከሩሲያ ተባርሮ ወደ ዩክሬን ተልኳል። ባለቤቱ አይሪና ቀደም ብላ ወደ ዩክሬን በመሄድ እዚያ ሲደርስ ተቀብላዋለች። ኮንስታንቲን ወደ ዩክሬን የተላከው ግንቦት 2020 የሩሲያ ዜግነቱን ስለተነጠቀ ነው።

ወንድም ኮንስታንቲን ባዠኖቭ ዩክሬን ገብቶ ከባለቤቱ ጋር እንደተገናኘ አንድ ባልና ሚስት የኢሳይያስ 54:17 ጥቅስ የሰፈረበት ፖስተር ይዘው ሲቀበሏቸው፤ ጥቅሱ “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል፤ . . . ይላል ይሖዋ” የሚል ነው

አጭር መግለጫ

ኮንስታንቲን የተወለደው ኖቭጎሮድ በተባለችው በምዕራባዊ ሩሲያ የምትገኝ ከተማ በ1975 ነው፤ ቤተሰቡ ሃይማኖተኞች አልነበሩም። ልጅ እያለ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ዩክሬን ሄደ። ኮንስታንቲን በወጣትነቱ ጂምናስቲክ እና ሙዚቃ ይወድ ነበር። ከሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመርቆ የሙዚቃ ባንድ መሪ ሆነ።

ኮንስታንቲን መጽሐፍ ቅዱስን ከመማሩ በፊትም እንኳ በዓመፅና በጦርነት መካፈል ተገቢ እንዳልሆነ ያምን ነበር። በመሆኑም በዩክሬን ጦር ሠራዊት ውስጥ እንዲያገለግል ሲመለመል ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። ኮሌጅ በነበረበት ጊዜ ስለ ሕይወትና ስለ ሃይማኖት ጥያቄዎች ነበሩት። የተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የሚያስተምሩትን ትምህርት መርምሯል፤ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ለጥያቄዎቹ መልስ አገኘ። በ1996 ተጠመቀ።

በ2001 ከአይሪና ጋር ትዳር መሠረተ። በጡብ ሥራ በተለይም ምድጃዎችን በመሥራት ሙያ ተሰማርቶ ራሱንና አይሪናን ያስተዳድር ነበር። በ2009 ወደ ሩሲያ ተዛወሩ።

ፍተሻ እና ማረፊያ ቤት

ሰኔ 12, 2018 መሣሪያ የታጠቁ የሩሲያ ልዩ ኃይሎች በሳራቶቭ የሚኖሩ ሰባት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በረበሩ፤ ከእነዚህ መካከል የኮንስታንቲን እና የአይሪና ቤትም ይገኝበታል። ኮንስታንቲን እና በሳራቶቭ የሚኖሩ ሌሎች ሁለት ወንድሞች ተይዘው ማረፊያ ቤት እንዲገቡ ተደረጉ።

ኮንስታንቲን ማረፊያ ቤት ሲገባ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ማጽናኛና ማበረታቻ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት አልቻለም። ኮንስታንቲን “ባለቤቴ ማስታወሻ ደብተር ላከችልኝ፤ እኔም የማስታውሳቸውን ጥቅሶች በየቀኑ እዚህ ደብተር ላይ እጽፍ ነበር” ብሏል። ይሖዋ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ 500 ጥቅሶች እንዲያስታውስ ረድቶታል! ኮንስታንቲን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያገኝ ደግሞ በአራት ወር ውስጥ ከዳር እስከ ዳር አነበበው። የአምላክ ቃል በእጅጉ አበረታው። ለባለቤቱና ለጓደኞቹ በሚልካቸው ደብዳቤዎች ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኛቸውን የሚያበረታቱ ሐሳቦች መጻፍም በጣም ያስደስተው ነበር።

ኮንስታንቲን ማረፊያ ቤት በነበረበት ወቅት ብዙ ጊዜ በተለይም ብቸኝነት ሲሰማውና ሚስቱ ስትናፍቀው ወደ ይሖዋ አጥብቆ ይጸልይ ነበር። እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “በጉልበቴ ተንበርክኬ እንባዬን እያፈሰስኩ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። አምላክን የጠየቅኳቸውን ነገሮች ወረቀት ላይ አሰፍራቸው ነበር፤ ከዚያም መልስ ያገኘሁላቸውን እሰርዛቸዋለሁ። ይሖዋ ከጎኔ እንዳልተለየ እርግጠኛ ነበርኩ።” ግንቦት 20, 2019 ኮንስታንቲን ከማረፊያ ቤት ተለቀቀ። ሆኖም መከራው በዚህ አላበቃም።

ፍርድ

መስከረም 19, 2019 ኮንስታንቲን እና በሳራቶቭ የሚኖሩ አምስት ወንድሞች ጥፋተኛ እንደሆኑ ተፈርዶባቸው እስር ቤት ወረዱ። እነዚህ ወንድሞች ያቀረቡት ይግባኝ ከጥቂት ወራት በኋላ ውድቅ ስለተደረገ አምስቱ ወንድሞች በኦረንበርግ ወደሚገኝ እስር ቤት ተዛወሩ። ኮንስታኒን ደግሞ ከቤቱና ባለቤቱ ከምትኖርበት ከሳራቶቭ ርቆ በዲሚትሮቭግራድ (ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ይርቃል) ወደሚገኝ እስር ቤት ተላከ።

ኮንስታንቲን የ2020⁠ን የመታሰቢያ በዓል እስር ቤት ውስጥ ሲያከብር

አይሪና ከኮንስታንቲን ጋር ተለያይታ በነበረችበት ወቅት JW ዜና ላይ የወጡና ስደትን በድፍረት እንዲሁም በደስታ የተቋቋሙ ወንድሞችና እህቶችን ተሞክሮ ማንበቧ አበረታቷታል። የኮንስታንቲን ቁርጠኝነት እና መረጋጋትም አጠናክሯታል። ኮንስታንቲን እስር ቤት እያለ ባደረገችው ቃለ ምልልስ ላይ “ምንጊዜም የሚናገረው አዎንታዊ ነገር ነበር!” ብላለች። ለኮንስታንቲን እንድትደውልለት ሲፈቀድላት አብረው ይዘምሩ፣ ይጸልዩና ያጠኑ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያደርጓቸው ውይይቶች በይሖዋ ላይ ያላትን እምነት እንዳጠናከሩላትና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም ደስታዋን ጠብቃ ለመኖር እንደረዷት ተናግራለች።

ኮንስታንቲን በእምነቱ ምክንያት በማረፊያ ቤት ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር በላይ፣ በእስር ቤት ደግሞ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ አሳልፏል። የተፈረደበትን የሦስት ዓመት ተኩል እስራት ለመጨረስ ዘጠኝ ወር ሲቀረው ተለቋል። ይህ የሆነው በማረፊያ ቤት ያሳለፈው ጊዜ ግምት ውስጥ ስለገባ ነው። በተጨማሪም የተፈታው በአመክሮ በመሆኑ የመጨረሻዎቹን ሁለት ወራት መታሰር አላስፈለገውም።

ኮንስታንቲን ከእስር ተፈትቶ ከአይሪና ጋር በመገናኘቱ ተደስተናል። ስደትን በጽናት እየተቋቋሙ ያሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሙሉ ንጉሥ ዳዊት በተናገረው “መከራው እስኪያልፍ ድረስ በክንፎችህ ጥላ ሥር እጠለላለሁ” በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ።—መዝሙር 57:1

a ኮንስታንቲን ከእስር ሲፈታ አይሪና እንዲሁም 20 ያህል ወንድሞችና እህቶች ተቀብለውታል፤ ከዚያም የውጭ አገር ሰዎች ወደ አገራቸው እስኪመለሱ ወደሚቆዩበት ጊዜያዊ ማቆያ ተወሰደ። ኮንስታንቲንን እንዲያጅቡ የተመደቡት ፖሊሶች ወደ ጊዜያዊ ማቆያው ከመወሰዱ በፊት ከባለቤቱ ጋር 30 ደቂቃ እንዲያሳልፍ ፈቅደውለት ነበር።