በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኮንስታንቲን ጉዜቭ

የካቲት 19, 2021
ሩሲያ

ወንድም ኮንስታንቲን ጉዜቭ በእምነቱ ምክንያት ተፈረደበት

ወንድም ኮንስታንቲን ጉዜቭ በእምነቱ ምክንያት ተፈረደበት

ወቅታዊ መረጃ | ወንድም ኮንስታንቲን ጉዜቭ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

ግንቦት 13, 2021 የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል ፍርድ ቤት ወንድም ኮንስታንቲን ጉዜቭ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። በመሆኑም በወንድም ኮንስታንቲን ጉዜቭ ላይ መጀመሪያ የተፈረደበት የሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስር በዚያው ይጸናል። እርግጥ በአሁኑ ወቅት ወንድም ኮንስታንቲን ጉዜቭ ወህኒ ቤት አይወርድም።

የፍርድ ውሳኔ

ሩሲያ ውስጥ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት የካቲት 18, 2021 በወንድም ኮንስታንቲን ጉዜቭ ላይ የሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት ፈርዶበታል። እርግጥ በአሁኑ ወቅት ወንድም ኮንስታንቲን ወህኒ ቤት አይወርድም።

አጭር መግለጫ

ኮንስታንቲን ጉዜቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1964 (ካባረቭስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ አባቱ ቤተሰቡን ይበድል የነበረ ከመሆኑም ሌላ የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ነበር። ኮንስታንቲን ስለ ሕይወት ዓላማ ጥያቄ ተፈጠረበት። ለጥያቄው መልስ ማግኘት ሲያቅተው የዕፅ እና የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ሆነ። ውሎ አድሮ ግን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ለጥያቄዎቹ የሚያረካ መልስ አገኘ። በሕይወቱ ውስጥ ሥር ነቀል ለውጥ አደረገ። በ2000 ተጠመቀ። በ2001 ከአናስታሲያ ጋር ትዳር መሠረተ

የክሱ ሂደት

ግንቦት 2018 ባለሥልጣናቱ “የፍርድ ቀን” የሚል ስያሜ በሰጡት ዘመቻ ቤቶችን በፈተሹበት ወቅት የኮንስታንቲንን ቤትም በርብረው ነበር። በዚህ ዘመቻ ላይ 150 ፖሊሶች በቢሮቢድዣን ከተማ የሚገኙ ቤቶችን በርብረዋል። ሐምሌ 29, 2019 ባለሥልጣናቱ በኮንስታንቲን ላይ የወንጀል ክስ መሠረቱ። ኮንስታንቲን ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች ስለመራ ብቻ “የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴዎች በማደራጀት” ወንጀል ተከሰሰ።

በዚህ ክልል ውስጥ በሚገኙ 22 የይሖዋ ምሥክሮች ላይ 19 የተለያዩ ክሶች ተመሥርተዋል፤ ክስ ከተመሠረተባቸው አንዷ የኮንስታንቲን ሚስት አናስታሲያ ናት።

በሩሲያ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ድፍረት በማሳየት የተዉት ምሳሌ፣ ኮንስታንቲን እና አናስታሲያም ደፋር እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። ኮንስታንቲን እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ እህቶች ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት፣ እዚያ ምንም እንደማይናገሩ ሲገልጹ በገዛ ጆሮዬ ሰምቼ ነበር። . . . ሆኖም የይሖዋ እርዳታና የወንድሞቻቸው ጸሎት፣ ግሩም በሆነ መንገድ እንዲናገሩና ለእምነታቸው ጥብቅና እንዲቆሙ ረድቷቸዋል።”

በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በሙሉ ምንጊዜም በጸሎታችን እናስባቸዋለን። እምነታቸውን ለማዳከም የሚሰነዘር ማንኛውም ዕቅድ እንደሚጨናገፍ እርግጠኞች ነን፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከእነሱ ጋር ነው።—ኢሳይያስ 8:10