በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ዬቭጌኒ ያኩ እና ባለቤቱ አይሪና

ግንቦት 17, 2021
ሩሲያ

ወንድም ዬቭጌኒ ያኩ የፍርድ ሂደቱን በሚከታተልበት ወቅት ጥበብ ለማግኘት በይሖዋ ታምኗል

ወንድም ዬቭጌኒ ያኩ የፍርድ ሂደቱን በሚከታተልበት ወቅት ጥበብ ለማግኘት በይሖዋ ታምኗል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ አደረገ

ጥቅምት 1, 2021 የአርሃንግዬልስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ዬቭጌኒ ያኩ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። የበታች ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ በዚያው ይጸናል።

ሐምሌ 19, 2021 በሶሎምባልስኪ የሚገኘው የአርሃንግዬልስክ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ዬቭጌኒ ያኩ ጥፋተኛ ነው የሚል ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን በድምሩ 880,000 ሩብል (12,082 የአሜሪካ ዶላር) መቀጫ እንዲከፍል ፈርዶበታል። ወንድም ዬቭጌኒ ወህኒ አይወርድም።

አጭር መግለጫ

ዬቭጌኒ ያኩ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1980 (ሶስኖቭዬትስ መንደር፣ ካሪላ ሩፑብሊክ)

  • ግለ ታሪክ፦ በአሥራዎቹ ዕድሜ በነበረበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ በጣም አስገረመው። በ2006 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ለመማር ሲል ወደ አርሃንግዬልስክ ተዛወረ። በ2007 ከአይሪና ጋር ትዳር መሠረተ። ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝና ከቤት ውጭ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስታቸዋል

የክሱ ሂደት

የካቲት 18, 2019 የሩሲያ ባለሥልጣናት የዬቭጌኒ ያኩን ቤት የበረበሩ ሲሆን “በጽንፈኝነት” እንቅስቃሴዎች ተካፍለሃል በሚል ያዙት። የአካባቢው ፖሊሶች ዬቭጌኒን አስረው ለሁለት ቀናት አቆዩት። በዚህ ወቅት ወዳጆቹና ቤተሰቡ ዬቭጌኒ የት እንዳለ የሚያውቁት ነገር አልነበረም።

ዬቭጌኒ ከተለቀቀ በኋላ ምሽት ላይ ከቤቱ እንዳይወጣ፣ በቤቱ ምንም ዓይነት ስብሰባ እንዳያደርግ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ሰዎች ጋር በስልክ፣ በኢ-ሜይል ወይም በኢንተርኔት እንዳይነጋገር ገደብ ተጣለበት። ከሰባት ወራት ገደማ በኋላ ፍርድ ቤቱ አንዳንዶቹን ገደቦች ያነሳለት ሲሆን ምሽት ላይ ከቤቱ መውጣትም ተፈቀደለት።

ኅዳር 25, 2019 ዬቭጌኒ “የጽንፈኝነት” እንቅስቃሴ አደራጅተሃል በሚል ተከሰሰ። ከዚያ በኋላም ተጨማሪ ክሶች ቀርበውበታል። ጥፋተኛ ተብሎ ከተፈረደበት እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊበየንበት ይችላል። ዬቭጌኒ በተሰነዘረበት ክስ የተነሳ ከሥራው ተባርሯል፣ የባንክ ሒሳቡን ማንቀሳቀስ እንዳይችል እገዳ ተጥሎበታል እንዲሁም ሁለት መኪኖቹ ተወርሰውበታል።

ወንድም ዬቭጌኒ እና አይሪና በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በይሖዋ ላይ ይበልጥ ተማምነዋል። አይሪና እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የምፈልገውን ነገር ለይቼ በመጥቀስ ላቀረብኩት ጸሎት የሰጠኝን መልስ እንዲሁም ለእኔና ለዤንያ [ለዬቭጌኒ] የሚያደርገውን እንክብካቤ ስመለከት ልቤ በከፍተኛ የአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል።”

ለምሳሌ አይሪና ባለቤቷ ፍርድ ቤት ሲቀርብ፣ መረጋጋትና እምነቱን ጥሩ አድርጎ ማስረዳት እንዲችል እንዲረዳው ወደ ይሖዋ ጸልያ ነበር። ዬቭጌኒም ተመሳሳይ ጸሎት አቅርቦ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በምርመራው ኮሚቴ ፊት ወይም ፍርድ ቤት በቀረብኩ ቁጥር ይሖዋ የሚያስፈልገኝን ጥበብ እንዲሰጠኝ እጠይቀው ነበር።” ዬቭጌኒ፣ ይሖዋ ጸሎቱን እንደመለሰለት ተሰምቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “መናገር የሚያስፈልገኝን ብቻ እንጂ ብዙ ነገር አላወራሁም። ይሖዋ ከጎኔ እንዳልተለየ አሳይቶኛል፤ እንዲሁም ጸሎቶቼን በማያሻማ መንገድ መልሶልኛል። አሁን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የእሱን እጅ በሕይወቴ ማየት ችያለሁ።”

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በምንጠባበቅበት ጊዜ ይሖዋ ለዬቭጌኒ ድፍረት እንደሚሰጠውና መከራከሪያውን “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ለማቅረብ እንደሚረዳው እንተማመናለን።—1 ጴጥሮስ 3:15