በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ዬቭጌኒ ጎሊክ ታኅሣሥ 2020 ከፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ቆሞ

ጥር 21, 2021
ሩሲያ

ወንድም ዬቭጌኒ ጎሊክ የገደብ እስራት ተበየነበት

ወንድም ዬቭጌኒ ጎሊክ የገደብ እስራት ተበየነበት

የፍርድ ውሳኔ

ሩሲያ ውስጥ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት ጥር 20, 2021 ወንድም ዬቭጌኒ ጎሊክ ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን አስተላለፈ። ወንድም ዬቭጌኒ ጎሊክ የሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስር ተበይኖበታል። እርግጥ እስር ቤት ገብቶ አይታሰርም። ወንድም ዬቭጌኒ ጎሊክ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ታውቋል።

አጭር መግለጫ

ዬቭጌኒ ጎሊክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1975 (ቢሮቢድዣን፣ የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ የብየዳ ባለሙያ ነው። የሚሠራው የውኃ ማሞቂያ ማሽኖች መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ ነው። የይሖዋ ምሥክር ከመሆኑ በፊት በሩሲያ ጦር ሠራዊት ውስጥ ያገለግል ነበር

    እውነትን የተማረው ከእናቱ ነው። ከሕይወት ዓላማ ጋር በተያያዘ ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ አገኘ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለሌሎች ይበልጥ አሳቢነት የሚያሳይ ሰው እንዲሆንም ረድቶታል

የክሱ ሂደት

ግንቦት 17, 2019 ማለዳ ላይ 150 የፌዴራል ደህንነት አባላት በሩሲያ ሩቅ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኘው በቢሮቢድዣን ከተማ የሚኖሩ ዘጠኝ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በረበሩ። ፖሊሶቹ ይህን ተልእኮ “የፍርድ ቀን” የሚል የኮድ ስም ሰጥተውት ነበር። የአካባቢው ባለሥልጣናት በወንድም ዬቭጌኒ ጎሊክና በዚያ የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል ውስጥ በሚኖሩ ሌሎች 21 ወንድሞችና እህቶች ላይ የወንጀል ክስ መሠረቱ። የፍርድ ሂደቱ የጀመረው ጥር 29, 2020 ነው።

አቃቤ ሕጉ ካቀረበው ማስረጃ መካከል ዬቭጌኒ መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ሲያጠና የተቀረጹ ቪዲዮዎች ይገኙበታል።

እንዲህ ያለውን ዓይን ያወጣ የፍትሕ ጥሰት መቋቋም ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ይሁንና ዬቭጌኒ እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ያለኝ መሆኑ በራሴ ላይ ሳይሆን በይሖዋ ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል። በአምላክ ቃል ውስጥ የማገኛቸው አበረታች ሐሳቦች ደስተኛ እንድሆን አድርገውኛል፤ ይህም እነዚህን ሐሳቦች ለሌሎች እንዳካፍል ያነሳሳኛል።”

ዬቭጌኒ በመዝሙር 23:4 ላይ ማሰላሰሉ በጣም ጠቅሞታል። ዬቭጌኒ እንዲህ ብሏል፦ “[ይህ ጥቅስ] ደፋር እንድሆንና በደስታ እንድጸና ረድቶኛል። የሞት አደጋ ቢደቀንብን እንኳ ይሖዋ ምንጊዜም ከአጠገባችን እንደሆነ እናውቃለን።”

ሌሎች የይሖዋ አገልጋዮችም ዬቭጌኒን ረድተውታል። እንዲህ ብሏል፦ “የፍርድ ሂደቱ በጀመረበት ወቅት ወንድሞችና እህቶች ፍርድ ቤት መጥተው ነበር፤ ይህም በእጅጉ አበረታቶኛል። በተጨማሪም ይሖዋ ግሩም የትዳር አጋር ሰጥቶኛል፤ እሷም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ረዳት ሆናልኛለች። ሁልጊዜ ደስተኛ ነኝ። የተትረፈረፈ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ምግብ እንዲሁም የሚያስፈልገኝን እርዳታ ሁሉ አግኝቻለሁ።”

ዬቭጌኒ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። እስካሁን ቀጥተኛ ስደት ላልደረሰባቸው ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “[የመንግሥቱን] መዝሙሮች በቃላችሁ አጥኑ፤ ጠላቶቻችሁን መውደድ ተማሩ፤ እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ደስተኛ የአምላክ አገልጋይ ለመሆን ራሳችሁን አሠልጥኑ።”

ሁላችንም በሩሲያ ከሚገኙ ወንድሞችና እህቶች መማራችንን እንቀጥል። ይሖዋ እነሱን በፈተና ወቅት እንዳበረታቸው ሁሉ እኛንም ያበረታናል።—መዝሙር 29:11