በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ወንድም ዲሚትሪ ማስሎቭ ከባለቤቱ ከዩሊያ ጋር

መጋቢት 18, 2021
ሩሲያ

ወንድም ዲሚትሪ ማስሎቭ ከጓደኞቹ ጋር መንፈሳዊ ነገሮችን በመወያየቱ እስራት ሊፈረድበት ይችላል

ወንድም ዲሚትሪ ማስሎቭ ከጓደኞቹ ጋር መንፈሳዊ ነገሮችን በመወያየቱ እስራት ሊፈረድበት ይችላል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ አደረገ

ጥቅምት 5, 2021 የክራስናያርስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት ዲሚትሪ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። መጀመሪያ ላይ የተጣለበት የገንዘብ ቅጣት በዚያው ይጸናል።

ሰኔ 2, 2021 በክራስናያርስክ ክልል የሚገኘው የሚኑሲንስክ ከተማ ፍርድ ቤት ወንድም ዲሚትሪ ማስሎቭ ጥፋተኛ ነው የሚል ውሳኔ አሳልፏል። ወንድም ዲሚትሪ ማስሎቭ የ450,000 ሩብል (6,125 የአሜሪካ ዶላር) ቅጣት ተጥሎበታል።

አጭር መግለጫ

ዲሚትሪ ማስሎቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1976 (ሚኑሲንስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ እናታቸው እሱን እንዲሁም ታናሽ ወንድሙንና ታናሽ እህቱን ያለአባት አሳድጋቸዋለች። ከሙያ ትምህርት ቤት በንብ እርባታ ሙያ በዲግሪ ተመርቋል። በአሁኑ ወቅት የቧንቧ ሠራተኛ ነው። ብስክሌት መንዳት፣ መዋኘት እንዲሁም አኮርዲዮን መጫወት ይወዳል

    ከልጅነቱ ጀምሮ ከሕይወት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ያሳስቡት ነበር። ለጥያቄዎቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽና አሳማኝ መልስ አገኘ። በ1994 ተጠመቀ። ለውትድርና አገልግሎት ሲመለመል ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት በመግለጽ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት መስጠት እንዲፈቀድለት ጠየቀ። በ1997 ከዩሊያ ጋር ትዳር መሠረተ

የክሱ ሂደት

ሚያዝያ 19, 2019 ምሽት ላይ ወታደሮች፣ የምርመራ ኮሚቴ አባላት እና የፌደራል ደህንነት አባላት በሚኑሲንስክ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አምስት ቤተሰቦችን ቤቶች ፈተሹ። በወቅቱ ፈታሾቹ አንድን የ76 ዓመት አረጋዊ ወንድም ገፍትረው ስለጣሏቸው ወንድም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከ30 በላይ ወንድሞችና እህቶች ለምርመራ በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር፤ እርግጥ በኋላ ላይ ተለቀዋል። ከጊዜ በኋላ በዲሚትሪ ላይ የወንጀል ክስ ተመሠረተበት። በዋነኝነት የተከሰሰው ከጓደኞቹ ጋር ተራራ የመውጣት ፕሮግራም አዘጋጅቶ በዚያ ወቅት ከእነሱ ጋር በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ በመወያየቱ ነው።

ዲሚትሪ በአሁኑ ወቅት የጉዞ ገደብ የተጣለበት ሲሆን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እየተጠባበቀ ነው። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነችው እናቱ ዲሚትሪ ወንጀለኛ እንዳልሆነና የተመሠረተበት የወንጀል ክስም ፍትሕ የጎደለው እንደሆነ ይሰማታል። የልጇ ሃይማኖት “ከየትኛውም ሃይማኖት ይበልጥ ሰላማዊ” እንደሆነ ገልጻለች።

ዲሚትሪ፣ ይሖዋ ለታማኞቹ ‘ብርታቱን እንደሚያሳይ’ ማወቁ መጽናኛና ድፍረት ሰጥቶታል።—2 ዜና መዋዕል 16:9