በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ዲሚትሪ ቪኖግራዶቭ ከባለቤቱ ከዣናርጉል እንዲሁም ከልጆቹ ከአሪና (በስተ ግራ) እና ከኦሌስያ (በስተ ቀኝ) ጋር

ግንቦት 18, 2021
ሩሲያ

ወንድም ዲሚትሪ ቪኖግራዶቭ ስደትን በጽናት ሲቋቋም የይሖዋ በረከት አልተለየውም

ወንድም ዲሚትሪ ቪኖግራዶቭ ስደትን በጽናት ሲቋቋም የይሖዋ በረከት አልተለየውም

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ አደረገ

ጥቅምት 28, 2021 የቼልያቢንስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ዲሚትሪ ቪኖግራዶቭ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ቀደም ሲል የተላለፈበት ፍርድ በዚያው ይጸናል። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርድም።

ሰኔ 7, 2021 በቼልያቢንስክ የሚገኘው የሴንትራልኒ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ዲሚትሪ ቪኖግራዶቭ ጥፋተኛ ነው የሚል ውሳኔ አሳለፈ። የሁለት ዓመት የገደብ እስር ተፈርዶበታል።

አጭር መግለጫ

ዲሚትሪ ቪኖግራዶቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1963 (ቼልያቢንስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ወላጆቹ ከተፋቱ በኋላ ያሳደገችው እናቱ ናት። ቼዝ መጫወት ይወድ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላም ይሄን ጨዋታ መተዳደሪያው አደረገው። በግል ትምህርት ቤት ውስጥ ቼዝ ያስተምራል። ከዣናርጉል ጋር በ1990 ትዳር መሠረተ። አራት ልጆች አሏቸው፤ የመጨረሻዎቹ ሁለት ልጆቻቸው አብረዋቸው ይኖራሉ

    ዲሚትሪ፣ ጥሩ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ፕላኔታችንን የሚበክሉትና ሌሎችን የሚጎዱት ለምን እንደሆነ ሁልጊዜ ያሳስበው ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አጥጋቢ መልስ አገኘ። በ2014 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

የክሱ ሂደት

በ2018 መገባደጃ አካባቢ ከመንግሥት የተላኩ ሰላዮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ያላቸው መስለው ዲሚትሪን ያነጋገሩት ጀመር። ጥር 2020 ባለሥልጣናቱ በዲሚትሪ ላይ የወንጀል ክስ ለመመሥረት በቂ “ማስረጃ” እንዳገኙ ገለጹ። ከሁለት ወራት በኋላ ፖሊሶች እሱ በሌለበት ቤቱን ፈተሹ።

ዲሚትሪ የማየት ችግር እንዲሁም የደም ግፊት አለበት። ሆኖም እንዲህ ብሏል፦ “ከአምላክ ጋር ያለኝ ዝምድና በአካላዊ ጤንነቴ ላይ የተመካ አይደለም። ፍርድ ቤት ቀርቤ ምሥክርነት መስጠት በመቻሌ ደስታና ኩራት ይሰማኛል።”

ዲሚትሪ እና ቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው የማንበብና የማሰላሰል እንዲሁም ለስብሰባዎች የመዘጋጀት፣ በስብሰባዎች ላይ የመገኘትና ሐሳብ የመስጠት ልማድ አላቸው። ለዓመታት ይህን ማድረጋቸው ከይሖዋ ጋርም ሆነ እርስ በርስ እንዲቀራረቡ እንዲሁም ስደትን ለመቋቋም ይበልጥ እንዲዘጋጁ ረድቷቸዋል። ዲሚትሪ እንዲህ ብሏል፦ “በዋነኝነት ከረዱን ነገሮች መካከል የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ጸሎት ይገኝበታል። ይሖዋ እነዚህ ጻድቃን የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል፤ ቤተሰባችንን አትረፍርፎ እየባረከው ነው።”

ስደትን በደስታ እየተቋቋሙ ካሉ ታማኝ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ብዙ እንማራለን። ስለ እነሱ ስናስብ በ2 ተሰሎንቄ 1:4 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ እናስተጋባለን፦ “እየደረሰባችሁ ያለውን ስደትና መከራ ሁሉ ችላችሁ በመኖር ባሳያችሁት ጽናትና እምነት የተነሳ በአምላክ ጉባኤዎች መካከል እኛ ራሳችን ስለ እናንተ በኩራት እንናገራለን።”