በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ዴኒስ አንቶኖቭ ከባለቤቱ ከኦልጋ ጋር (በስተ ግራ) እንዲሁም ወንድም አሌክሳንደር ኮሮሌቭ ከባለቤቱ ከናታሊያ ጋር (በስተ ቀኝ) ከእስር እንደተለቀቁ

ሰኔ 19, 2024
ሩሲያ

ወንድም ዴኒስ አንቶኖቭ እና ወንድም አሌክሳንደር ኮሮሌቭ ከእስር ተፈቱ

ወንድም ዴኒስ አንቶኖቭ እና ወንድም አሌክሳንደር ኮሮሌቭ ከእስር ተፈቱ

ሰኔ 14, 2024 ወንድም ዴኒስ አንቶኖቭ እና ወንድም አሌክሳንደር ኮሮሌቭ ሩሲያ ውስጥ ሞሎችኒትሳ በተባለ መንደር ከሚገኝ እስር ቤት ተለቀቁ። ሁለቱም ወንድሞች ነሐሴ 25, 2022 ጥፋተኛ ተብለው የሁለት ዓመት እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወሳል። ማረፊያ ቤት ያሳለፉት ጊዜ ታሳቢ ተደርጎ የእስር ጊዜያቸው ተጠናቅቋል።

የዴኒስ ባለቤት ኦልጋ ከባሏ ጋር ተለያይተው በቆዩበት ጊዜ ምን እንዳበረታታቸው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የያዙ ደብዳቤዎችን በመላላክ እርስ በርስ እንበረታታ ነበር። በጣም የረዳን አንዱ ጥቅስ መክብብ 8:12 ላይ የሚገኘው ‘እውነተኛውን አምላክ የሚፈሩ ሰዎች አምላክን በመፍራታቸው የኋላ ኋላ መልካም እንደሚሆንላቸው ተረድቻለሁ’ የሚለው ጥቅስ ነው። ይህ ጥቅስ፣ ተስፋ ቆርጠን ይሖዋን ማገልገላችንን እስካልተውን ድረስ ይሖዋ እንድንጸና የሚረዳ ብርታት እንደሚሰጠን አረጋግጦልናል።”

አሌክሳንደር ፍርዱን ከመስማቱ በፊት ለችሎቱ በሰጠው የመጨረሻ ቃል ላይ ያለበትን ሁኔታ ከነቢዩ ዳንኤል ጋር አነጻጽሮ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ዳንኤል ሞት ሊያስከትልበት እንደሚችል ቢያውቅም እንኳ እምነቱ ወደ ይሖዋ አምላክ መጸለዩን እንዲቀጥል አነሳስቶታል። እኔም በስደት የማይበገር እንዲህ የመሰለ እምነት እንዲኖረኝ መጸለዬን እቀጥላለሁ።”

ዴኒስ እና አሌክሳንደር ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመቀላቀላቸው ተደስተናል። የእነሱ ተሞክሮ በመዝሙር 4:3 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ተስፋ እውነተኝነት ያረጋግጥልናል፤ “ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሆነውን ሰው ልዩ በሆነ መንገድ እንደሚይዘው እወቁ፤ ይሖዋ [በጠራነው] ጊዜ [ይሰማናል]።”