በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 24, 2020
ሩሲያ

ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ልዩ የቅጣት ክፍል እንዲገባ ተደረገ

ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ልዩ የቅጣት ክፍል እንዲገባ ተደረገ

ሐምሌ 15, 2020 ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ልዩ የቅጣት ክፍል (ሺዞ) እንዲገባ ተደረገ። ቢያንስ እስከ ሐምሌ 27 ድረስ እዚያ እንደሚቆይ ይጠበቃል። ይህ ውሳኔ የተላለፈው ወንድም ክሪስተንሰን ከዚያ እንዲወጣ ከተደረገ ከአራት ቀን በኋላ ነው። ወንድም ክሪስተንሰን ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ሺዞ ከተላከ “የእስር ቤቱን ሕግ ሆን ብሎ የሚጥስ ዓመፀኛ” እንደሆነ ተቆጥሮ እስር ቤቱ እስከ ስድስት ወር ያህል ከባድ ቅጣት ወደሚሰጥበት ልዩ የቅጣት ክፍል (ኢፒኬቲ) ሊያስገባው ይችላል። የወንድም ክሪስተንሰን ጠበቆች ይህ ውሳኔ እንዲቀየር ይግባኝ ለመጠየቅ አስበዋል።

ባለሥልጣናቱ ወንድም ክሪስተንሰንን እየቀጡት ያሉት በእስር ቤት ውስጥ የተሰጠውን ሥራ አላከናወነም በሚል ነው። የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ወንድም ክሪስተንሰን እስር ቤት ውስጥ በሚገኘው የልብስ ስፌት ፋብሪካ እንዲሠራ አዘው ነበር። ሆኖም እስር ቤት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የጤንነት ሁኔታው እያሽቆለቆለ ይገኛል። የእስር ቤቱ ሐኪሞች ወንድም ክሪስተንሰን በየመሃሉ እረፍትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እስካደረገ ድረስ የጤንነቱ ሁኔታ ሥራውን ለማከናወን እንደሚፈቅድለት ተናግረዋል። ሆኖም ለእስር ቤቱ የማይሠራ ሌላ ሐኪም ቀደም ሲል ወንድም ክሪስተንሰንን መርምሮት የነበረ ሲሆን የጤንነቱ ሁኔታ ሥራውን ለማከናወን እንደማይፈቅድለት ገልጾ ነበር።

ሺዞ ውስጥ የታሰሩ እስረኞች ምግብ መግዛት፣ ስልክ መደወል ወይም መቀበል፣ ጠያቂዎችን ማነጋገር እንዲሁም የሚላክላቸውን ዕቃ መቀበል አይፈቀድላቸውም። ሕጉ እዚህ ክፍል ውስጥ የታሰሩ እስረኞች ከሃይማኖታዊ አገልጋዮች ጋር እንዲገናኙ ይፈቅዳል። ወንድም ክሪስተንሰን ግን የጉባኤ ሽማግሌዎች መጥተው እንዲያነጋግሩት መጠየቅ አይችልም። ምክንያቱም ሩሲያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የነበራቸውን ሕጋዊ እውቅና አጥተዋል።

ቀደም ሲል ሪፖርት እንዳደረግነው፣ ሐምሌ 23 የልጎፍ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ክሪስተንሰን ከእስር ጊዜው ቀደም ብሎ እንዲፈታና ቀሪው ጊዜ በገንዘብ ቅጣት እንዲተካለት ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን አቃቤ ሕጉ ይህ ውሳኔ እንዲቀየር ይግባኝ ጠየቀ። የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ከአቃቤ ሕጉ ጋር በመተባበር የወንድም ክሪስተንሰንን ስም ለማጥፋትና ከእስር ጊዜው ቀደም ብሎ እንዲፈታ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ለመከላከል እየሞከሩ ያሉ ይመስላል።

ወንድም ክሪስተንሰንም ሆነ ባለቤቱ አይሪና አሁንም አዎንታዊ አመለካከት አላቸው። ይሖዋ ምንጊዜም ታማኝ አገልጋዮቹ ከባድ ፈተናዎችን ጭምር በትዕግሥትና በደስታ እንዲወጡ እንደሚረዳ ማየት በጣም ያበረታታል።—ቆላስይስ 1:11