በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ አሌክሲ ቡደንቹክ፣ አሌክሲ ሚረትስኪ፣ ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ፣ ጀናዲ ጀርመን እና ሮማን ግሪዳሶቭ

የካቲት 24, 2020
ሩሲያ

ወንድሞች በሩሲያ እስር ቤት የተደበደቡ የእምነት አጋሮቻቸውን ለመርዳት ሄዱ

ወንድሞች በሩሲያ እስር ቤት የተደበደቡ የእምነት አጋሮቻቸውን ለመርዳት ሄዱ

በኦረንበርግ፣ ሩሲያ ውስጥ የታሠሩ አምስት ወንድሞቻችን ክፉኛ እንደተደበደቡ የሚገልጸው ዜና ልክ እንደወጣ በዚያ ከተማ ያሉ ወንድሞች እነሱን ለመርዳት ወደ እስር ቤቱ ሄደዋል። የታሠሩት ወንድሞች ይኸውም አሌክሲ ቡደንቹክ፣ ጀናዲ ጀርመን፣ ሮማን ግሪዳሶቭ፣ ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ እና አሌክሲ ሚረትስኪ ከኦረንበርግ 800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሳራቶቭ ነዋሪዎች ናቸው።

ወንድም ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ ፈገግ ብሎ፤ ይህ ፎቶግራፍ የተነሳው ወንድም ማክሃማዲየቭ በእስር ቤት ጠባቂዎች ክፉኛ ከተደበደበ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው፤ የለበሰው ጃኬት ቁስሉን ሸፍኖታል

የካቲት 15, 2020 ኢንተርኔት ላይ በወጡ የዜና ሪፖርቶች ላይ እንደተገለጸው በኦረንበርግ የታሠሩትን አምስት የሳራቶቭ ወንድሞች የእስር ቤቱ ጠባቂዎች በዱላ ደብድበዋቸዋል። በአቅራቢያው የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ዜናውን እንዳነበቡ ወዲያውኑ ወደ እስር ቤቱ ሄዱ። የራሳቸውን ነፃነት አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን በድፍረት ተናገሩ። እነዚህ ወንድሞች ስለ አምስቱ ወንድሞች ደኅንነት እንዲነግሯቸው የእስር ቤቱን ተረኛ ጠባቂዎች ጠየቋቸው። ወንድም ማክሃማዲየቭ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበትና ሆስፒታል እንደገባ በመስማታቸው በሕይወት መኖሩን ለማረጋገጥ ጥያቄ አቅርበዋል። እነዚህ ወንድሞች ከጠባቂዎቹ ጋር ለሁለት ሰዓታት ያህል ተነጋግረዋል።

በኦረንበርግ የሚኖሩ ወንድሞች በእስር ላይ ላሉት ወንድሞች፣ ለሚስቶቻቸውና ለጠበቆቻቸው ቀጣይ እርዳታ የሚሰጥ ቡድን አደራጅተዋል። የኦረንበርግ ወንድሞች አስር ቤት ላሉት ወንድሞች በየጊዜው አበረታች ደብዳቤዎች የሚጽፉላቸው ከመሆኑም ሌላ በእስር ቤት ውስጥ የማይገኙ ጤናማ ምግቦችን መግዛት እንዲችሉ ገንዘብ አሰባስበውላቸዋል።

ወንድሞችና እህቶች ያላቸው ፍቅር እንዲሁም የሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ለእስር ቤቱ ሠራተኞች ግሩም ምሥክርነት ሰጥቷል። የይሖዋ ምሥክሮች በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ለሚኖሩና ጨርሶ ለማያውቋቸው የእምነት ባልንጀሮቻቸው ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው ማስተዋል ችለዋል።

ወንድሞቻችን በዕብራውያን 13:3 ላይ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ማወቃችን በጣም ያበረታታናል፦ “በእስር ላይ ያሉትን ከእነሱ ጋር ታስራችሁ እንዳላችሁ አድርጋችሁ በማሰብ ሁልጊዜ አስታውሷቸው፤ እናንተም ራሳችሁ ገና በሥጋ ያላችሁ በመሆናችሁ እንግልት እየደረሰባቸው ያሉትን አስቡ።”