ሚያዝያ 12, 2021
ሩሲያ
ዓለም አቀፍ የመታሰቢያ ማኅበር ወደ ሳይቤሪያ የተጋዙትን በሶቪየት የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች 70ኛ ዓመት ለማሰብ ኮንፈረንስ አካሄደ
ወደ ሳይቤሪያ የተጋዙትን የይሖዋ ምሥክሮች 70ኛ ዓመት ለማሰብ ሚያዝያ 1, 2021 በሞስኮ ጋዜጣዊ መግለጫ ከተሰጠ ከጥቂት ቀናት በኋላ ማለትም ሚያዝያ 6 ላይ ዓለም አቀፉ የመታሰቢያ ማኅበር ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀ ኮንፈረንስ አካሂዷል፤ በኮንፈረንሱ ላይ የተለያዩ የሩሲያ ምሁራንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተጋብዘው ነበር። ንግግር ያቀረቡት ሰዎች በ1951 ስለተካሄደው፣ ሶቪየቶች ኦፐሬሽን ኖርዝ ብለው ስለሚጠሩት ዘመቻ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በተጨማሪም በሩሲያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዘመናት ስለተቋቋሙት ስደት ገልጸዋል።
ኦፐሬሽን ኖርዝ የተባለውን ዘመቻ ያስተባበረው የሶቪየት የአገር ደህንነት ሚኒስቴር ነው። በ1951 መጀመሪያ አካባቢ ሚኒስቴሩ የሶቪየት ኅብረት መሪ ለነበረው ለጆሴፍ ስታሊን የሚከተለውን መልእክት የላከ ሲሆን መልእክቱ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “በሶቪየት ኅብረት ላይ በማመፅ በሚስጥር የሚንቀሳቀሱትን ጅሆቫዎች ለማጥፋት የሶቪየት ኅብረቱ የደህንነት ሚኒስቴር የዚህን ኑፋቄ ቡድን መሪዎች ማሰር እንዲሁም በዩክሬን፣ በቤላሩስ፣ በሞልዶቫ፣ በላትቪያ፣ በሊትዌኒያ እና በኢስቶኒያ የሚኖሩ ጅሆቫዎችን ከነቤተሰቦቻቸው ወደ ኢርኩትስክ እና ቶምስክ ክልሎች ማጋዝ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል።” በአጠቃላይ ከ3,000 በሚበልጡ ቤተሰቦች ውስጥ ያሉ ወደ 10,000 የሚጠጉ ሰዎች በግዞት ተወስደዋል። በሶቪየት ኅብረት ታሪክ ውስጥ በሃይማኖት ምክንያት ከተደረጉ የግዞት ዘመቻዎች ሁሉ ይህ ትልቁ ነው።
የኮንፈረንሱ መሪ የሆኑት አሌክሳንደር ጉርያኖቭ በስብሰባው መክፈቻ ላይ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “በዚህ ሃይማኖት ቡድን ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ስደት . . . አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ስለዚህ እዚህ ወቅት ላይ ስለ ኦፐሬሽን ኖርዝ መዘከራችን በጣም አስፈላጊ ነው።”
የታሪክ ምሁርና የጂኦግራፊ ተመራማሪ የሆኑት እንዲሁም በሶቪየት ኅብረት በተካሄዱ የግዳጅ ግዞቶች ላይ ከፍተኛ ጥናት ያደረጉት ፓቬል ፖሊያን በሶቪየት ኅብረት ስለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ እንዲሁም ከተካሄደባቸው የግዞት ዘመቻ በስተጀርባ ስላለው ምክንያት መግለጫ ሰጥተዋል። በ1940ዎቹ መጨረሻ እና በ1950ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የደህንነት ሚኒስቴሩ የይሖዋ ምሥክሮች በጣም የተዳራጁ ሰዎች እንደሆኑ አስተውሎ ነበር። በተጨማሪም አቶ ፖሊያን እንዲህ ብለዋል፦ “[የይሖዋ ምሥክሮች] የተዋጣላቸው ሚስዮናውያን ናቸው፤ ይህ ደግሞ አምላክ የለሽ የሆኑትን የመንግሥት ባለሥልጣናት አላስደሰታቸውም።”
የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የሞስኮ ሄልሲንኪ ግሩፕ ተባባሪ ኃላፊ የሆኑት ቫሌሪ ቦርሼቭ የሶቪየት ባለሥልጣናት ፕሮፓጋንዳዎችንና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም የይሖዋ ምሥክሮችን “ለማንቃት” ስላደረጉት ጥረት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በጊዜ ሂደት “ባለሥልጣናቱ ልፋታቸው ሁሉ ከንቱ እንደሆነና ምንም ውጤት እንዳላስገኘ ተገነዘቡ” በማለት አቶ ቦርሼቭ ተናግረዋል። አክለውም “የይሖዋ ምሥክሮች አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። ከአቋማቸው ፍንክች አላሉም” ብለዋል።
የመታሰቢያ ሰብዓዊ መብቶች ማዕከል ምክር ቤት እና የምክር ቤቱ የፖለቲካ እስረኞች ድጋፍ ፕሮግራም መሪ የሆኑት ሰርጌ ዴቪዲስ በሩሲያ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለሚደርሰው ስደት መግለጫ ሰጥተዋል፤ ይህ ስደት ከ1998 አንስቶ እየተባባሰ መጥቷል። አቶ ሰርጌ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሚያዝያ 2017 ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ ማዕከላት ለመዝጋት ስላደረገው ውሳኔ የተናገሩ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው የይሖዋ ምሥክሮች ብቸኛው እውነተኛ ሃይማኖት እነሱ ብቻ እንደሆኑ ስለሚናገሩ እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “የተመሠረተባቸው ክስ መሠረተ ቢስ እንደሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም የየትኛውም ሃይማኖት ተከታዮች ቢሆኑ እውነትን የያዙት እነሱ ብቻ እንደሆኑ ያምናሉ።”
የአውሮፓ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ተወካይ የሆነው ወንድም ያሮስላቭ ሲቩልስኪ በግዞት የተወሰዱት የይሖዋ ምሥክሮች በሳይቤሪያ ያጋጠሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች በተመለከተ ከወላጆቹ የሰማውን ለአድማጮች ተናግሯል። አንዳንድ ቤተሰቦች በዚያ ከባድ ቅዝቃዜ ያለመኖሪያ ቤት ጫካ ውስጥ እንዲኖሩ ተደርገው ነበር። ወንድሞች የሚኖሩበት ቦታ ለማግኘት መሬቱን ቆፍረው መጠለያ ሠርተው ነበር። የተሻለ ቦታ እስኪያገኙ ድረስ በዚያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለወራት ኖረዋል። የይሖዋ ምሥክሮቹ ጫካ ውስጥ ሲኖሩ በአብዛኛው የሚመገቡት ሳማ እና የዛፍ ቅርፊት ነበር። አብዛኞቹ በረሃብ ወይም በበሽታ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
ወንድም ሲቩልስኪ የይሖዋ ምሥክሮች በ1951 በግዞት የተወሰዱበት ምክንያት በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ለስደት ከተዳረጉበት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተናግሯል። ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካ ገለልተኛ በመሆን የያዙትን አቋም በተሳሳተ መንገድ ስለሚረዱት ለመንግሥት ሥልጣን እውቅና እንደማይሰጡ ይሰማቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ለሥልጣን ባላቸው አክብሮት ተለይተው የሚታወቁ እንዲሁም ሕግ አክባሪና ጠንካራ ሠራተኛ የሆኑ ዜጎች እንደሆኑ ይዘነጉታል።
የኮንፈረንሱ መሪ የሆኑት አሌክሳንደር ጉርያኖቭ በመደምደሚያ ንግግራቸው ላይ በአሁኑ ጊዜ በሩሲያ ስላለው ሁኔታ አጭር መግለጫ ሰጥተዋል። “መንግሥት ለዚህ የሃይማኖት ቡድን ተከታዮች ለየት ያለ ጥላቻ ያለው ይመስላል” በማለት ተናግረዋል። በተጨማሪም አድማጮች የግዞት ዘመቻው ከተካሄደ ከ70 ዓመታት በኋላ ታሪክ ራሱን እየደገመ እንዳለ ማስታወስ እንዳለባቸው ገልጸዋል። ሕግ አክባሪ የሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን ሃይማኖታዊ ነፃነት ተጠቅመው ስላመለኩ ብቻ ዳግመኛ ወንጀለኛ ተብለው ስደት እየደረሰባቸው ነው።
ኮንፈረንሱን የሚያሳየውን ቪዲዮ ኢንተርኔት ላይ በሩሲያኛ ብቻ ማግኘት ይቻላል።