በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በ2019 የአካባቢው ፖሊስና የፌዴራል ደህንነት አባላት በኒዥኒ ኖቭጎሮድ የሚኖርን የአንድ ወንድማችንን ቤት ሲፈትሹ

ሐምሌ 15, 2020
ሩሲያ

የሩሲያ ባለሥልጣናት በበርካታ ወንድሞቻችን ቤቶች ላይ ፍተሻ አካሄዱ

የሩሲያ ባለሥልጣናት በበርካታ ወንድሞቻችን ቤቶች ላይ ፍተሻ አካሄዱ

አንድ የዜና ዘገባ እንደገለጸው መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ሐምሌ 13, 2020 በቮሮኒሽ ክልል በሚገኙ የ110 ወንድሞቻችን ቤቶች ላይ ፍተሻ አካሂደዋል። ይህ ቁጥር ከ2017 አንስቶ በይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ከተካሄዱ የፍተሻ ዘመቻዎች ሁሉ ከፍተኛው ነው። አሌክሳንድር ቦኮቭ እና ዲሚትሪ ካቲሮቭ የተባሉ ሁለት ወንድሞች የሞባይላቸውን የይለፍ ቃል ለፖሊሶቹ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተደበደቡ ከመሆኑም ሌላ ለውርደት ተዳርገዋል።

ይህ የፍተሻ ዘመቻ እንዲካሄድ ያዘዘው በቮሮኒሽ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ነው። ፖሊሶቹ በአካባቢው ባሉ ቢያንስ ሰባት ከተሞችና መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን ፈትሸዋል። በርካታ ወንድሞቻችን በዚያ አካባቢ ወዳለ የምርመራ ቢሮ ተወስደዋል።

በቀጣዩ ቀን ማለትም ሐምሌ 14, 2020 የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት የሚከተሉት አሥር ወንድሞች እስከ መስከረም 3, 2020 ድረስ ችሎት ፊት ሳይቀርቡ እንዲታሰሩ አዟል፦ የ44 ዓመቱ አሌክሴ አንቲዩኪን፣ የ47 ዓመቱ ሰርጌ ባዬቭ፣ የ44 ዓመቱ ዩሪ ጋልካ፣ የ56 ዓመቱ ቫልዬሪ ጉርስኪ፣ የ41 ዓመቱ ቪታሊ ኔሩሽ፣ የ24 ዓመቱ ስቴፓን ፓንክራቶቭ፣ የ54 ዓመቱ ኢጎር ፖፖቭ፣ የ44 ዓመቱ ዬቭጌኒ ሶኮሎቭ፣ የ51 ዓመቱ ሚካኼል ቬሴሎቭና የ51 ዓመቱ አናቶሊ ያጉፖቭ።

ከላይ የጠቀስነው ሪፖርት የገለጸው 110 ቤቶች እንደተፈተሹ ቢሆንም እስካሁን ድረስ 100 የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ቤታቸውና ሌሎች ንብረቶቻቸው እንደተፈተሹባቸው ማረጋገጥ ችለናል። ይህ ቁጥር ሊጨምር ይችላል። ቤታቸው የተፈተሸባቸውን ወንድሞች ሁሉ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም ስልኮቻቸውና ኮምፒውተሮቻቸው በፍተሻው ወቅት ተወስደውባቸዋል።

ከዚህ ቀደም በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ የፍተሻ ቁጥር የተመዘገበው የካቲት 10, 2020 ሲሆን በዚያን ዕለት ባለሥልጣናቱ በትራንስባይካል ክልል በሚገኙ የ50 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ፍተሻ አካሂደዋል። በ2017 ከተላለፈው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ወዲህ ከ1,000 በሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ፍተሻ ተካሂዷል።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አንጻር በሩሲያም ሆነ በሌሎች አገሮች በሚገኙ ወንድሞቻችን ላይ ከባድ ፈተና እየደረሰባቸው መሆኑ አያስገርመንም። ይሖዋ ወንድሞቻችን ታማኝ ሆነው ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጣቸው በመተማመን ለእነሱ መጸለያችንን እንቀጥላለን።—1 ጴጥሮስ 4:12-14, 19