በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 1, 2020
ሩሲያ

የሩሲያ አቃቤ ሕግ ወንድም ክሪስተንሰን ከእስር ጊዜው ቀድሞ እንዲለቀቅ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን አገደ

የሩሲያ አቃቤ ሕግ ወንድም ክሪስተንሰን ከእስር ጊዜው ቀድሞ እንዲለቀቅ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን አገደ

ሰኔ 26, 2020 የልጎፍ እስር ቤት ባለሥልጣናት ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን አስቸጋሪ ወንጀለኞች ብቻ በሚታሰሩበት ልዩ የቅጣት ክፍል ውስጥ እንዲቆይ በማድረግ ሕግ ተላልፈዋል። የወንድም ክሪስተንሰን የጤንነት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ከመሄዱ አንጻር ይህ እርምጃ እሱን ለማዳከም ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስላል። በተጨማሪም አቃቤ ሕጉ ወንድም ክሪስተንሰን ከእስር ጊዜው ቀድሞ እንዲለቀቅ የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዳይሆን ለማድረግ ሲል ሌሎች መሠረተ ቢስ ክሶችን እየተጠቀመ ሳይሆን አይቀርም፤ ከጥቂት ቀናት በፊት አቃቤ ሕጉ ራሱ ይህን ውሳኔ ደግፎ ነበር።

ወንድም ክሪስተንሰን ከተላለፈበት የስድስት ዓመት እስራት ፍርድ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ጨርሷል። በአመክሮ ለመለቀቅ ወይም የእስር ጊዜው ሳያልቅ ለመፈታት የሚያስፈልገውን መሥፈርት ካሟላ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። ከዚህ በፊት ያስገባቸው ሦስት ማመልከቻዎች ምንም ምላሽ ሳያገኙ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ አራተኛው ማመልከቻ ወደ ፍርድ ቤት ተላለፈለት። ሰኔ 23, 2020 የልጎፍ አውራጃ ፍርድ ቤት ቀሪው የእስር ጊዜ በገንዘብ ቅጣት እንዲለወጥለት አዘዘ። የአመክሮው ጥያቄ በፍርድ ቤት በተሰማበት ወቅት በዚያ የነበሩት አርተም ኮፋኖቭ የተባሉ አቃቤ ሕግ የቅጣት ማቅለያውን ደግፈው ነበር።

ከሁለት ቀን በኋላ አሌክሴ ሻቱኖቭ የተባሉ ሌላ አቃቤ ሕግ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሕገ ወጥ እንደሆነ በመናገር ውሳኔው እንዲሰረዝና በዚያው ፍርድ ቤት ሌላ ዳኛ በተገኘበት ጉዳዩ ድጋሚ እንዲታይ ጥያቄ አቀረቡ። አቶ ሻቱኖቭ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት የልጎፍ እስር ቤት አስተዳደር ወንድም ክሪስተንሰን “በማረሚያ ቤት ውስጥ ያሳየው የሥራ ሥነ ምግባርና ማኅበራዊ ሕይወት” ጥሩ እንዳልሆነ ያቀረበውን ሪፖርት መሠረት በማድረግ ነው።

ሰኔ 23 የወንድም ክሪስተንሰን የአመክሮ ጥያቄ በፍርድ ቤት በተሰማበት ወቅት የእስር ቤቱ ተወካዮች ተመሳሳይ ክስ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ዳኛው ክሱ መሠረተ ቢስ እንደሆነ በመናገር ውድቅ አድርገውት ነበር። የወንድም ክሪስተንሰን ጠበቃ፣ ወንድም ክሪስተንሰን የጤና እክል ስላለበት በእስር ቤት ውስጥ የጉልበት ሥራ መሥራት እንደማይችል የሚያረጋግጡ የሕክምና ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርበው ነበር። የእስር ቤት ተወካዮቹ የምሥክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ የወንድም ክሪስተንሰንን የጤና ሁኔታ ያገናዘበ ሥራ ሊሰጡት እንደማይችሉ አምነዋል።

የአቃቤ ሕግ ቢሮው ወንድም ክሪስተንሰን ቀደም ብሎ እንዲለቀቅ ይግባኝ መጠየቅ በጀመረበት ጊዜ የእስር ቤት ባለሥልጣናቱ በወንድም ክሪስተንሰን ላይ ሁለት ክሶች መሠረቱ። የመጀመሪያው ክስ በተሳሳተ ሰዓት በመመገቢያ አዳራሽ ተገኝቷል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በወታደሮች ሰፈር ጃኬት ሳይደርብ ካናቴራ ብቻ ለብሶ ታይቷል የሚል ነው። በዚህ የተነሳ የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ወንድም ክሪስተንሰንን ለአሥር ቀን ያህል በልዩ የቅጣት ክፍል ውስጥ እንዲቆይ አድርገዋል። በሩሲያ ሕግ መሠረት ባለሥልጣናቱ እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰድ የሚችሉት አንድ እስረኛ የእስር ቤት ሕጎችን በተደጋጋሚ በመጣስ ከባድ ጥፋት ሲያጠፋ ነው፤ እስረኛው ከባድ ጥፋት ቢያጠፋም እንኳ ባለሥልጣናቱ እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰድ የሚችሉት እስረኛው የሕክምና ምርመራ ካደረገ በኋላ ብቻ ነው። ከወንድም ክሪስተንሰን ጋር በተያያዘ ግን እነዚህ መሥፈርቶች ስላልተሟሉ በልዩ የቅጣት ክፍል ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችል ምንም መሠረት አልነበራቸውም።

ወንድም ክሪስተንሰን የታሰረው ሦስት ሜትር በሁለት ሜትር ስፋት ባለው ክፍል ውስጥ ሲሆን ሌላ እስረኛም አብሮት ታስሯል። ክፍሉ የታፈነና ሻጋታ ያለው መሆኑ የወንድም ክሪስተንሰን የጤና ችግር እንዲባባስ የሚያደርግ ነው። ከጥቂት ወራት በፊት በሳንባ ምች የተያዘ ከመሆኑም ሌላ ከባድ የህብለ ሰረሰር ችግር እንዳለበት በምርመራ ታውቋል። የወንድም ክሪስተንሰን ጠበቃ እንዳለው “የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁ ቢሆንም የማይመች አልጋ ላይ እንዲተኛ አድርገዋል፤ ይህም ለከባድ ሥቃይ ዳርጎታል።”

ወንድም ክሪስተንሰን ሕጎቹን ተላልፏል በተባለበት ጊዜ ሌሎች እስረኞችም አብረውት የነበሩ ቢሆንም ወደ ልዩ የቅጣት ክፍል የተላከው እሱ ብቻ እንደሆነ ለጠበቃው ነግሯቸዋል። የወንድም ክሪስተንሰን ጠበቃ “ሁኔታው ወንድም ዴኒስ በፍርድ ቤት ትእዛዝ መሠረት እንዳይፈታ ለማገድ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ድርጊት ነው ብለን እንድንደመድም ያደርገናል” ብለዋል።

የሩሲያ ባለሥልጣናት ወንድሞቻችንን ለማጥቃት መሠሪ የሆኑ አዳዲስ ዘዴዎችን መቀየሳቸውን ቢቀጥሉም ይሖዋ ለወንድሞቻችን አስተማማኝ መጠጊያ እንደሚሆናቸው እርግጠኞች ነን። ይሖዋ ወንድም ክሪስተንሰንንና ባለቤቱን አይሪናን በዚህ ፈታኝ ጊዜ ታማኝ ሆነው ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንዲሰጣቸው ምንጊዜም እንጸልያለን።—መዝሙር 94:13, 21, 22