በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ አናቶሊ ራዝዶባሮቭ እና ባለቤቱ ግሬታ እንዲሁም ኒኮላይ ሜሪኖቭ እና ባለቤቱ ሊልያ በሩሲያ ወታደሮች ጥቃት ሳይደርስባቸው በፊት

ጥቅምት 10, 2021
ሩሲያ

የሩሲያ ወታደሮች ሁለት ባለትዳሮች ላይ ጥቃት ፈጸሙ

የሩሲያ ወታደሮች ሁለት ባለትዳሮች ላይ ጥቃት ፈጸሙ

ሰኞ ጥቅምት 4, 2021 የታጠቁ የሩሲያ ወታደሮች a በወንድም አናቶሊ እና በእህት ግሬታ ራዝዶባሮቭ እንዲሁም በወንድም ኒኮላይ እና በእህት ሊልያ ሜሪኖቭ ላይ የኃይል ጥቃት ፈጽመዋል። ይህ አረመኔያዊ ጥቃት የተፈጸመው የወታደሮች ብርጌድ በኢርኩትስክ ከተማ ባሉ 12 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ያካሄደውን ብርበራ ተከትሎ ነው። ወታደሮቹ በዚህ ዘመቻ ወቅት ሌሎች በርካታ ወንድሞችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

ንጋት 12:00 ሰዓት ላይ ወታደሮች የአናቶሊን እና የግሬታን ቤት ሰብረው ገቡ። ግሬታን በፀጉሯ እየጎተቱ ወደ ሌላ ክፍል ከወሰዷት በኋላ እጇን ወደ ኋላ አስረው ደበደቧት።

አናቶሊን ደግሞ መሬት ላይ ዘርረው እጁን በካቴና ወደኋላ አሰሩት፤ እንዲሁም ጭንቅላቱንና ሆዱን መቱት። ከዚያም ወታደሮቹ ወደኋላ የታሰሩትን እጆቹን አንጠልጥለው ከመሬት ምንጭቅ አድርገው አነሱት። በዚህ ጊዜ አናቶሊ የሰውነቱ ክብደት ትከሻው ላይ ስላረፈ ለከፍተኛ ሥቃይ ተዳረገ። ወታደሮቹ፣ አናቶሊ ጥፋተኛ መሆኑን እንዲያምንና ስለ ወንድሞች መረጃ እንዲሰጣቸው ለማስገደድ እጁን ይመቱት ጀመር። በተጨማሪም ጠርሙስ በፊንጢጣው ለማስገባት በመሞከር አሠቃዩት። ወታደሮቹ በእነዚህ ባልና ሚስት ቤት ከስምንት ሰዓት በላይ ቆይተዋል።

ወታደሮች የኒኮላይን እና የሊልያን ቤት ሰብረው ሲገቡ በመጀመሪያ ኒኮላይን በከባድ ነገር ፊቱን መቱት። ራሱን ስቶ መሬት ላይ ተዘረረ። ኒኮላይ ሲነቃ አንድ ወታደር ላዩ ላይ ቁጭ ብሎ እየደበደበው ነበር። ወታደሩ የኒኮላይን የፊት ጥርሶች ሰበረበት። ሊልያን ደግሞ በፀጉሯ ይዘው እየጎተቱ ከአልጋዋ ላይ አወረዷት፤ ከዚያም በካቴና አሰሯት። በቅጡ ለመልበስ እንኳ ዕድል ሳይሰጧት ደበደቧት።

ወታደሮቹ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም የፈጸሙት ይህ የጭካኔ ድርጊት በሩሲያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው። በተጨማሪም የሩሲያ መንግሥት፣ በግለሰቦች ላይ አካላዊ ጥቃት መፈጸምን የሚከላከሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያወጧቸውን ሕጎች የመታዘዝ ግዴታ አለበት። በመሆኑም እነዚህ ባለትዳሮች በአገሪቱም ሆነ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በማቅረብ ፍትሕ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።

ማረፊያ ቤት እንዲገቡ በፍርድ ቤት የተበየነባቸውን ስድስት ወንድሞች ለማበረታታት 300 ወንድሞችና እህቶች በኢርኩትስክ ወደሚገኘው ኦክትያቢርስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት መጥተው ነበር፤ ይህ የሆነው ወታደሮች በኢርኩትስክ ከተማ ባሉ 12 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ብርበራ ባካሄዱና በሁለት ባለትዳሮች ላይ ጥቃት በፈጸሙ ማግስት ነው

ከዘመቻው በኋላ በነበሩት ሁለት ቀናት ስድስት ወንድሞች ማረፊያ ቤት እንዲገቡ ፍርድ ቤት በይኖባቸዋል፤ እነሱም ያሮስላቭ ካሊን፣ ሰርጌ ኮስትዬቭ፣ ኒኮላይ ማርቲኖቭ፣ ሚካኼል ሞይሽ፣ አሌክሲ ሶልኔችኒ እና አንድሬ ቶልማቼቭ ናቸው። እንዲህ ያለ ግፍ ለደረሰባቸው የእምነት አጋሮቻቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድጋፋቸውን ለማሳየት 300 ያህል ወንድሞችና እህቶች ወደ ፍርድ ቤቱ ሄደዋል።

ሩሲያ ላሉ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሙሉ ልክ እንደ ጳውሎስ እንዲህ ልንላቸው እንፈልጋለን፦ “እየደረሰባችሁ ያለውን ስደትና መከራ ሁሉ ችላችሁ በመኖር ባሳያችሁት ጽናትና እምነት የተነሳ በአምላክ ጉባኤዎች መካከል እኛ ራሳችን ስለ እናንተ በኩራት እንናገራለን።”—2 ተሰሎንቄ 1:4

a የሩሲያ ብሔራዊ ዘብ ተንቀሳቃሽ ልዩ ኃይል