ሚያዝያ 19, 2022
ሩሲያ
የሩሲያ ወንድሞቻችን ላለፉት አምስት ዓመታት እገዳ ውስጥ ቢሆኑም ደፋሮችና ድል አድራጊዎች ናቸው
የሩሲያ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ላይ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ እገዳ ከጣለ ሚያዝያ 20, 2022 አምስት ዓመት ሞላው። a እገዳው ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ የሩሲያ ባለሥልጣናት ስደቱን ይበልጥ አፋፍመውታል፤ ወንድሞቻችንን ያሠቃዩበት ጊዜም አለ። ያም ቢሆን jw.org ላይ የሚወጡት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በድፍረት ጸንተዋል።
ወደ አምስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር የቆየው ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን ግሩም ምሳሌ ትቷል። ግንቦት 2019 ይግባኙ ውድቅ በተደረገበት ወቅት ፍርድ ቤት ውስጥ እሱን ለመደገፍ ለሄዱት ወንድሞችና እህቶች በእርጋታና በልበ ሙሉነት እንዲህ አላቸው፦ “አቅሜ በፈቀደው መጠን ይሖዋን ለማገልገል ጥረት አድርጌያለሁ። ለዘላለም ይህን ማድረጌን እቀጥላለሁ።”
ወንድም ኢጎር ቱሪክም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ቆርጧል። በሶቪየት ግዛት ወቅት ስደት ከደረሰበት ከወንድም ኒኮላይ ካሊባባ ጋር በአንድ ወቅት ተገናኝቶ ነበር። ኒኮላይ የአምላክ ሕዝቦች ፈተና ሲደርስባቸው የይሖዋን እርዳታ የሚያዩበት አጋጣሚ እንደሚያገኙ ለኢጎር ነግሮት ነበር። ኢጎር “በእምነታችን ምክንያት መከራ መቀበል ትልቅ መብት እንደሆነ ግልጽ ሆነልኝ” ብሏል። ኢጎር የሰባት ዓመት እስራት ተፈርዶበት እስር ቤት ውስጥ ቢሆንም በጽናት ቀጥሏል።
ወንድም ዬቭጌኒ ፌዲን ቁርጥ ውሳኔውን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ለራሳችን ፍትሕ ለማግኘት የምንታገልበት ጊዜ አይደለም። ምሥክርነት መስጠት አለብን፤ ይሖዋ ፍትሕ እንድናገኝ ያደርጋል። የምንታገለው በረከት ለማግኘት ነው። . . . ስለ እነዚህ ነገሮች ማሰቤ የፈተናዎቹ ውጤት ምንም ይሁን ምን ለሚደርሱብኝ ፈተናዎች ተገቢ አመለካከት እንዲኖረኝ ይረዳኛል። እያንዳንዱ ፈተና ይሖዋን ለማስከበርና ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጠናል።”
እህት ታትያና ዡክም በተመሳሳይ እንዲህ ብላለች፦ “እስካሁን የተቋቋምናቸውን ነገሮች ስናስብ ወደፊትም ፈተናዎቹን በጽናት ለመቋቋም ያለን ቁርጠኝነት ይጨምራል። ይህም ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነ ያረጋግጣል። የሰማዩ አባታችን ባይረዳን ኖሮ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ደስታችንን መጠበቅ አንችልም ነበር።”
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዬቭጌኒ እንዲህ ብሏል፦ “ድል አድራጊዎች ነን! ማረፊያ ቤት ስንገባ የምንወጣው ድል አድርገን ነው። ፍርድ ቤት ስንሄድ የምንወጣው ድል አድርገን ነው። እስር ቤት ስንገባ የምንወጣው ድል አድርገን ነው።”
የታሪክ ምሁር የሆኑትና በሶቪየት ኅብረት ስለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ያጠኑት ዶክተር ኤሚሊ ባራን በ2017 እገዳው መጣሉ ከመገለጹ በፊት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ወደፊት የሚሆነውን ነገር ካለፈው ታሪክ ተነስተን እንገምት ካልን ሩሲያ የይሖዋ ምሥክሮችን ማጥፋት እንደማትችል መናገር እንችላለን።”
በኢሳይያስ 54:17 በሩሲያና በክራይሚያ ካሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በተያያዘ እውነት መሆኑ ታይቷል፤ በእርግጥም “[እነሱን] ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል።”
a ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ባሳለፈበት ወቅት የሩሲያ መንግሥት፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸውን ሕጋዊ ተቋማት ቢያፈርስም እንኳ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ግለሰቦች እምነታቸውን ማራመድ እንደሚችሉ ገልጾ ነበር። ሆኖም መንግሥት እያደረገ ያለው ነገር ከዚህ ሐሳብ ጋር ይቃረናል።