በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቅርቡ ሕይወቱ ያለፈው ወንድም ኢጎር አቭራሜንኮ ከባለቤቱ ከዬሌና ጋር

መጋቢት 30, 2020
ሩሲያ

የሩሲያ የፌዴራል ደህንነት ፖሊሶች የሟች ወንድማችንን ቤት በረበሩ

የሩሲያ የፌዴራል ደህንነት ፖሊሶች የሟች ወንድማችንን ቤት በረበሩ

በካባረቭስክ ክልል የሚገኙ የፌዴራል ደህንነት ፖሊሶች መጋቢት 23, 2020 የወንድም ኢጎር አቭራሜንኮን ቤት በረበሩ፤ በዚህ ወቅት ወንድም አቭራሜንኮ በልብ ድካም ሕይወቱ ካለፈ ስድስት ቀኑ ነበር። ፖሊሶቹ የያዙት በወንድም ኢጎር አቭራሜንኮ ስም የተዘጋጀ ማዘዣ ቢሆንም ኮምፒውተርንና ካሜራን ጨምሮ የባለቤቱ የዬሌና የግል ንብረት የሆኑ የተለያዩ ዕቃዎችን ወስደዋል።

በዚያ ቀን ፖሊሶች ወደ ዬሌና የሥራ ቦታ በመሄድ አጅበው ወደ ቤቷ ወሰዷት፤ በዚያም ዋና መርማሪ የሆነው ስታኒስላቭ ግሬቤንኪን የፍተሻ ማዘዣ ይዞ ጠበቃት። እህት ዬሌና ባለቤቷ መሞቱን ለመርማሪው ገለጸችለት። እሱም ባለቤቷ መሞቱን እንደሚያውቅ፣ ሆኖም የፍተሻ ማዘዣው የወጣው የወንድም ኢጎር አቭራሜንኮ ሞት ከመታወቁ በፊት በመሆኑ ፍተሻው መካሄድ እንዳለበት ነገራት።

መርማሪው ፖሊሶቹ ቀለል ያለ ፍተሻ ብቻ እንደሚያደርጉና እንዲህ የሚያደርጉት “ፋይሉን ቶሎ ዘግተው ወደ መዝገብ ቤት ለማስገባት” መሆኑን ተናገረ። ሆኖም ፖሊሶቹ ቤቱን አብጠርጥረው መፈተሽ ጀመሩ።

በካባረቭስክ ክልል በአሥር የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ክስ ተመሥርቷል። የሩሲያ ባለሥልጣናት የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን እምነት ለማዳከም ጥረት ማድረጋቸውን ቢቀጥሉም የእምነት አጋሮቻችን በአፍቃሪው አባታችን በይሖዋ ‘ተማምነው በመኖር ብርቱ መሆናቸውን እንደሚያሳዩ’ እርግጠኞች ነን።—ኢሳይያስ 30:15