በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 17, 2020 ወንድም ሩስላን አልዬቭ ከባለቤቱ ከክርስቲና ጋር ፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ቆሞ

ታኅሣሥ 17, 2020
ሩሲያ

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም ሩስላን አልዬቭ ላይ የገደብ እስር በይኗል

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም ሩስላን አልዬቭ ላይ የገደብ እስር በይኗል

ወንድም አልዬቭ የሰጠው ተጨማሪ ሐሳብ በዚህ ዜና ላይ ተካቷል

ታኅሣሥ 17, 2020 በሮስቶቭ-ኦን-ዶን ከተማ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም ሩስላን አልዬቭ ላይ የሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስር በይኗል። በእርግጥ ወንድም ሩስላን እስር ቤት አይገባም።

ወንድም ሩስላን ፍርዱን እየተጠባበቀ በነበረባቸው ቀናት “የአምላክ ሰላም” እንዳለው በግልጽ ይታይ ነበር። (ፊልጵስዩስ 4:7) በተረጋጋ መንፈስ ጓደኞቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምንም ይሁን ምን እኔን አያስጨንቀኝም። አምላክ የፈቀደው ማንኛውም ነገር በእሱ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ አውቃለሁ። ደግሞም በሚያስፈልገኝ ጊዜ ይረዳኛል። ታሰርኩም አልታሰርኩ ይሖዋን ማገልገሌን እቀጥላለሁ።” በተጨማሪም ሩስላን በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቹና እህቶቹ በታማኝነት እንዲጸና እንደሚጸልዩለት ያውቃል፤ የእነሱ ጸሎት “ትልቅ መጽናኛ” እንደሆነለት ተናግሯል።

ታኅሣሥ 14, 2020 ወንድም ሩስላን ለፍርድ ቤቱ በተናገረው የመጨረሻ ሐሳብ ላይ በድፍረት እንዲህ ብሏል፦ “በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም አንድ የ33 ዓመት ወጣት በመንግሥት ላይ ዓመፅ ቀስቅሰሃል በሚል ክስ ተወንጅሎ ችሎት ፊት ቀርቦ ነበር። ሆኖም የክስ ሂደቱ እንደሚያሳየው ይህ ሰው የተፈረደበት ከአምላኩ ከይሖዋ ጋር ባለው ዝምድና የተነሳ ነው። የምሥክሮቹ ቃል እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው፤ በተጨማሪም ጥፋተኝነቱን የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ አልቀረበም። ያም ሆኖ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ተፈርዶበታል። ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

“እኔም ዛሬ፣ በሃያ አንደኛው መቶ ዘመን ላይ በ33 ዓመቴ በተመሳሳይ ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ወንጀል ተከስሼ ችሎት ፊት ቆሜያለሁ። . . . ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ወንጀል እንደተከሰስኩ ስሰማ፣ ይህ መሠረተ ቢስ የሆነና ፈጽሞ የማይመስል ክስ በጣም አስገርሞኛል።”

ከዚህም በተጨማሪ ሩስላን የዘርና የሃይማኖት ጥላቻን በማነሳሳት ወንጀል የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል። እንዲህ ብሏል፦ “በተለያዩ ሁኔታዎች የተነሳ ቢያንስ የሦስት ሕዝቦችን ማለትም የሩሲያን፣ የአዘርባጃንንና የዩክሬንን ሕዝቦች ባሕል እያየሁ ነው ያደግኩት። የሦስቱንም ሕዝቦች ባሕል በእኩል ደረጃ እወዳለሁ። . . . በተጨማሪም እንግሊዝኛ ተናጋሪ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች የመጡ እንዲሁም ቻይንኛ የሚናገሩ ብዙ ጓደኞች አሉኝ። . . . እኔ የአዘርባጃን ተወላጅ ነኝ። በአዘርባጃንና በአርሜንያ ሕዝቦች መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጥላቻ እንዳለ ሁሉም ሰው ጠንቅቆ ያውቃል፤ የእኔ የቅርብ ጓደኛ ግን አርሜንያዊ ሲሆን በሠርጌ ዕለትም ምሥክር ነበር። የተለያየ ብሔር፣ ዘር፣ ሃይማኖትና የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች እንድወድ ያስተማረኝ ሃይማኖቴ ነው። . . . ከዚህ አንጻር፣ የተለያየ ዘርና ብሔር ባላቸው ሰዎች መካከል ጥላቻን በማነሳሳት ወይም አንዱ ዘር ከሌላው ዘር ይበልጣል የሚለውን አስተሳሰብ በማራመድ ወንጀል መከሰሴ እኔንም ሆነ የሚያውቁኝን ሰዎች በጣም አስገርሞናል።”

በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ችሎት ፊት ሲቀርቡ፣ ያገኙትን አጋጣሚ በድፍረት ምሥክርነት ለመስጠት መጠቀማቸው በጣም አበረታቶናል። በባለሥልጣናት ፊት ለእምነታችን ስንሟገት የምንዘራውን የእውነት ዘር ይሖዋ እንደሚባርከው እንተማመናለን።—ማቴዎስ 10:18