በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ

ግንቦት 20, 2021
ሩሲያ

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ላይ የሁለት ዓመት ተኩል እስራት ፈረደበት

በእምነቱ ምክንያት ለሦስተኛ ጊዜ ታስሯል

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ላይ የሁለት ዓመት ተኩል እስራት ፈረደበት

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

ነሐሴ 5, 2021 የሳራቶቭ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል፤ ሆኖም ከዚህ በፊት የተፈረደበትን የሁለት ዓመት ተኩል እስራት ወደ ሁለት ዓመት ከአራት ወር ዝቅ አድርጎለታል። በቅርቡ፣ ፍርድ ከተላለፈበት ከግንቦት 20, 2021 ጀምሮ ከቆየበት ማረፊያ ቤት ወደ እስር ቤት ይወሰዳል።

ግንቦት 20, 2021 በሳራቶቭ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ጥፋተኛ ነው በማለት የሁለት ዓመት ተኩል እስር ፈርዶበታል። ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት ተወስዷል።

አጭር መግለጫ

ሩስታም ሴድኩሌቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (አሽጋባት፣ ቱርክሜኒስታን)

  • ግለ ታሪክ፦ ያሳደገችው እናቱ ነች። በ1993 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከሁለት ዓመት በኋላ እናቱም ማጥናት ጀመረች። በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናው ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ስላልፈቀደለት ከመጠመቁ በፊት ቱርክሜኒስታን ውስጥ ሁለት ጊዜ ታስሯል

    የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸውንና መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክር መያዙን ሲመለከት በ1998 ራሱን ወስኖ ተጠመቀ። የሩስታም እንጀራ አባት የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ምክንያት ከአገር ተባረረ፤ ስለዚህ በ2000 መላው ቤተሰብ ወደ ሩሲያ ተዛወረ

    የስልክ ቴክኒሺያንና የግንባታ ባለሙያ ሆኖ ሠርቷል። ከባለቤቱ ከዩሊያ ጋር የተገናኙት በ2001 ነው። ባልና ሚስቱ ቦውሊንግ መጫወት፣ ሽርሽር መሄድና የጠረጴዛ ቴኒስ መጫወት ይወዳሉ። ከመስከረም 2019 ወዲህ የሩስታምን ወላጆች የሚንከባከቡት እነሱ ናቸው

የክሱ ሂደት

መጋቢት 2019 አንድ የፌዴራል ደህንነት አባል ወደ ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭና ወደ ባለቤቱ ወደ ዩሊያ ቤት መጣ። ደጃፋቸውን በመኪናው ከዘጋው በኋላ ሁለቱንም ለየብቻ የወንጀል ምርመራ አደረገባቸው፤ ከዚያም ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ፌዴራል ደህንነት ቢሮ እንዲመጡ አዘዛቸው።

የካቲት 15, 2020 ሩስታምና ዩሊያ አንድ የገበያ ማዕከል ውስጥ ሳሉ ፖሊሶች ያዟቸው። ሩስታም ማረፊያ ቤት ተወሰደ። በኋላም ፍርድ ቤቱ በቁም እስር እንዲቆይ አዘዘ። መጀመሪያ ላይ ለሁለት ወራት ያህል በአንድ ተቋም እንዲቆይ ተደረገ፤ በዚያ በነበረበት ወቅት ባለቤቱን ማግኘት አይፈቀድለትም ነበር። ወደ ቤቱ እንዲገባ ከተፈቀደለት በኋላ ደግሞ ኢንተርኔትም ሆነ ከቤት ውጭ ያሉ ሰዎችን ማግኘት የሚያስችል ማንኛውም ዘዴ እንዳይጠቀም ታገደ። የቁም እስር ቆይታው ሰባት ጊዜ ያህል ተራዝሟል። ሩስታም በአጠቃላይ በቁም እስር 217 ቀን አሳልፏል።

ሩስታም በቁም እስር በነበረበት ወቅት ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። በአንዳንድ ወቅቶች ከቤት ወጥቶ በእግር መንሸራሸር የሚፈቀድለት ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት ብቻ ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ግቢውን ለመንከባከብም ሆነ ጣሪያውን ለመጠገን ከቤት መውጣት አይፈቀድለትም ነበር። አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ የረዳው ምን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የቁም እስር፣ ለመጸለይና ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ለማሰላሰል ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቶኛል። በሥራ መጠመዴና አስቀድሜ የዕለቱን ፕሮግራም ማውጣቴ በጭንቀት እንዳልዋጥ ረድቶኛል። አንዳንዶቹ የእምነት ባልንጀሮቼ እስር ቤት ውስጥ ከእኔ እጅግ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አውቅ ነበር።”

ሩስታም ከዚያ ቀደም ካጋጠሙት ፈተናዎችም ብርታት አግኝቷል። በቱርክሜኒስታን ታስሮ ስለነበረበት ጊዜ ሲያስታውስ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ደግፎኛል፤ በተለይ በወጣትነቴ ታስሬ በነበረበት ጊዜ ረድቶኛል። ይህም በእሱ ሙሉ በሙሉ እንድተማመንና እንድረጋጋ ረድቶኛል።”

ሩስታም በይሖዋ አገልግሎት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ማድረጉን ቀጥሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ስብሰባ መቅረትም ሆነ መንፈሳዊ ልማዳችንን ቸል ማለት የለብንም። እንዲሁም ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች፣ ለመስበክና ወንድሞቻችንን ለማበረታታት ያለንን ውስን ጊዜ እንዲሻሙብን ልንፈቅድ አይገባም። ይሖዋ በመደበኝ ቦታ አቅሜ በፈቀደ መጠን በእሱ አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ፤ ምክንያቱም የቀረው ጊዜ በጣም አጭር ነው።”

ይሖዋ በሩሲያ ያሉ ታማኝ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ‘ፈቃዱን እንዲያደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ እንደሚያስታጥቃቸው’ እርግጠኞች ነን።—ዕብራውያን 13:21