በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሰርጌይ ክሊሞቭ ግንቦት 2019 በፍርድ ቤት የእስረኞች ማቆያ ክፍል ውስጥ ሆኖ

ኅዳር 11, 2019
ሩሲያ

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም ሰርጌይ ክሊሞቭ ላይ የስድስት ዓመት እስር በየነ፤ ከ2017 አንስቶ ይህን ያህል ከባድ ፍርድ የተበየነበት የይሖዋ ምሥክር የለም

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም ሰርጌይ ክሊሞቭ ላይ የስድስት ዓመት እስር በየነ፤ ከ2017 አንስቶ ይህን ያህል ከባድ ፍርድ የተበየነበት የይሖዋ ምሥክር የለም

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ አደረገ

ጥር 27, 2022 ስምንተኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወንድም ሰርጌይ ክሊሞቭ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ወንድም ክሊሞቭ አሁንም እስር ቤት ይገኛል።

ኅዳር 5, 2019 በቶምስክ ከተማ የሚገኘው የኦክትያብርስኪይ አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም ሰርጌይ ክሊሞቭ ላይ የስድስት ዓመት እስር ፈረደ። ሩሲያ ውስጥ ይህን ያህል ርዝመት ያለው እስር የተፈረደበት ዴኒስ ክሪስተንሰን ብቻ ነበር። ሆኖም ፍርድ ቤቱ በወንድም ሰርጌይ ላይ ተጨማሪ ገደቦችን ጥሎበታል፤ በመሆኑም የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2017 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ ከጣለበት ጊዜ አንስቶ የወንድም ሰርጌይን ያህል ከባድ ፍርድ የተበየነበት የይሖዋ ምሥክር የለም።

ወንድም ሰርጌይ የታሰረው ሰኔ 3, 2018 ፖሊሶችና ወታደሮች የሁለት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በፈተሹበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ አንዲትን የ83 ዓመት እህት ጨምሮ 30 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ነበር። ሆኖም ከወንድም ሰርጌይ በቀር ሁሉም ተለቀቁ። በወንድም ሰርጌይ ላይ ግን ክስ የተመሠረተበት ሲሆን ፍርድ ቤቱ ለሁለት ወራት ያህል ፍርድ ሳይበየንበት በእስር እንዲቆይ አዘዘ። የእስር ቆይታው ሰባት ጊዜ ተራዝሞ ነበር፤ በመሆኑም የስድስት ዓመት ብይኑ ከመጀመሩ በፊት ለአንድ ዓመት ከአምስት ወር ያህል ከባለቤቱና ከቤተሰቡ ተለይቶ በእስር ቆይቷል።

የወንድም ሰርጌይ ጠበቆች ፍርድ ቤቱን ይግባኝ ይጠይቃሉ። በተጨማሪም ወንድም ሰርጌይ ፍርድ ሳይበየንበት በእስር እንዲቆይ ከመገደዱ ጋር በተያያዘ ነሐሴ 20, 2018 ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቤቱታ ቀርቦ ነበር።

በ2019 ሩሲያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸው እንደተፈተሸና እንደታሰሩ የሚገልጹ መረጃዎች ከበፊቱ ይበልጥ ጨምረዋል። ያም ቢሆን ወንድሞቻችን ታማኝነትና ድፍረት ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። ወንድሞቻችን በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመናቸው የእሱ በረከት እንዳልተለያቸው ማወቃችን ያበረታታናል።—መዝሙር 56:1-5, 9