በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 24, 2020
ሩሲያ

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም ሰርጌ ለደንዮቭ ላይ የሁለት ዓመት የገደብ እስራት በየነ

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም ሰርጌ ለደንዮቭ ላይ የሁለት ዓመት የገደብ እስራት በየነ

ኅዳር 24, 2020 በካምቻትካ ክልል የሚገኘው የፔትሮፓቭሎቭስክ-ካምቻትስኪ ከተማ ፍርድ ቤት ወንድም ሰርጌ ለደንዮቭ ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን አስተላልፏል። በመሆኑም ሁለት ዓመት የገደብ እስራት ከሦስት ዓመት የፈተና ጊዜ ጋር ተፈርዶበታል። አሁን እስር ቤት መግባት አያስፈልገውም።

በችሎቱ የመጨረሻ ቀን ላይ ወንድም ሰርጌ የይሖዋ ምሥክር መሆን ምን ማለት እንደሆነ በድፍረት አብራርቶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ የአንድ ሕዝብ፣ ድርጅት ወይም እምነት ስም አይደለም። ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ‘ምሥክሮቼ’ በማለት ጠርቷቸዋል። ይህንን ጥቅስ መሠረት በማድረግ፣ በ1931 በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ‘የይሖዋ ምሥክሮች’ ተብለን መጠራት ጀመርን። ይህ ስም፣ የአምላክ ምሥክሮች የመሆን ሥራ እንደተሰጠን የሚያሳይ ነው፤ ይህ ሥራ ፈጣሪ፣ አዳኝና የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የሆነው አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው አስደናቂ ዓላማ ለሌሎች መናገርን የሚጠይቅ ነው። እኔም ሆንኩ የእምነት አጋሮቼ ይህንን እንደ ታላቅ መብት ነው የምንቆጥረው።”—ኢሳይያስ 43:10

ወንድም ሰርጌ “ወንጀል እንደፈጸመ ሰው የማፍርበት ምንም ምክንያት የለም። ሕሊናዬ በአምላክም በሰውም ዘንድ ንጹሕ ነው” በማለት ለፍርድ ቤቱ በእርግጠኝነት ተናግሯል።