ታኅሣሥ 17, 2019
ሩሲያ
የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም አሉሽኪን ላይ የስድስት ዓመት እስር ፈረደበት፤ ሌሎች አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ በአመክሮ እንዲቆዩ ወስኗል
በፔንዛ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 13, 2019 ዓርብ ጠዋት በወንድም ቭላዲሚር አሉሽኪን ላይ የስድስት ዓመት እስር ፈረደ። ወንድም አሉሽኪን ወዲያውኑ በካቴና ታስሮ ወደ እስር ቤት ተወሰደ። የወንድም አሉሽኪን ባለቤት የሆነችውን ታትያናን ጨምሮ አምስት ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር። ፍርድ ቤቱ አምስቱም የይሖዋ ምሥክሮች (ሦስት ወንድሞችና ሁለት እህቶች) በአመክሮ እንዲቆዩና ጥፋት ካጠፉ ለሁለት ዓመት እንዲታሰሩ በይኗል። በፔንዛ የሚኖሩት ስድስቱም ወንድሞችና እህቶች ይግባኝ ይጠይቃሉ።
ቀደም ሲል በሌላ ዜና ላይ እንደተገለጸው ወንድም አሉሽኪን ተይዞ የታሰረው ሐምሌ 15, 2018 ነበር፤ በዚያ ዕለት ጭምብል ያጠለቁና ጠመንጃ የታጠቁ በርካታ ፖሊሶች ወደ ቤቱ መጥተው ነበር። ፖሊሶቹ ለአራት ሰዓት ያህል ቤቱን የፈተሹ ሲሆን ተንቀሳቃሽ ስልኮችን፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን፣ መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወስደዋል። በዚያው ቀን ፖሊሶች የይሖዋ ምሥክሮች የሚኖሩባቸውን ሌሎች አምስት ቤቶች የፈተሹ ከመሆኑም ሌላ 40 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችንና እህቶችን ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደዋል።
ፖሊሶቹ ወንድም አሉሽኪን ለሁለት ቀናት በጊዜያዊ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ካደረጉ በኋላ በፔንዛ የሚገኘው የፒርቮማይስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም አሉሽኪን ጉዳዩ እስኪታይ ድረስ ለሁለት ወራት በእስር ቤት እንዲቆይ ወሰነ። በኋላም የአውራጃው ፍርድ ቤት ወንድም አሉሽኪን ያለፍርድ በእስር የሚቆይበት ጊዜ ከአንዴም ሁለቴ እንዲራዘም አድርጓል። ወንድም አሉሽኪን ወደ ስድስት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ያለፍርድ ከታሰረ በኋላ በቁም እስር እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን ፍርድ ቤት እስከቀረበበት እስከ ታኅሣሥ 13 ድረስ በዚህ ሁኔታ ቆይቷል።
ከወንድም አሉሽኪን ጋር ተመሳሳይ ክስ ከቀረበባቸው አምስት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ሦስቱ ቭላዲሚር ኩልያሶቭ፣ አንድሬ ማግሊቭ እና ዴኒስ ቲሞሺን ናቸው። እነዚህ ሦስት ወንድሞች የወንጀል ምርመራውና የፍርድ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቁም እስር ቆይተዋል። የቀሩት ሁለቱ ማለትም እህት ታትያና አሉሽኪና እና እህት ጋሊያ ኦልኮቫ ደግሞ ከየካቲት 2019 አንስቶ ከሌሎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነትና በእንቅስቃሴያቸው ላይ ገደብ ተጥሎባቸው ነበር።
ነሐሴ 2019 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድን (ዎርኪንግ ግሩፕ ኦን አርቢትራሪ ዲቴንሽን) ሩሲያ ወንድም አሉሽኪንን ማሰሯ አግባብ እንዳልሆነ የሚገልጽ የ12 ገጽ ሪፖርት አዘጋጅቶ ነበር። ሪፖርቱ እንዲህ ይላል፦ “አጣሪ ቡድኑ አቶ አሉሽኪን በቁጥጥር ሥር መዋልም ሆነ ያለፍርድ መታሰር እንዳልነበረባቸውና ከዚህ በኋላም ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደማይገባ ያምናል። . . . ይህን ኢፍትሐዊ ድርጊት ማስቆም የሚቻልበት ትክክለኛው መንገድ አቶ አሉሽኪንን በአፋጣኝ መልቀቅ [ነው።]” የስድስቱ ወንድሞችና እህቶች ጠበቆች መከላከያቸውን ለፍርድ ቤቱ ለማቅረብ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን ይህን ሪፖርት ተጠቅመው ነበር። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ታኅሣሥ 13 ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት ዳኛው ከአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ ለማገድ በ2017 ያሳለፈው ውሳኔ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሩሲያ በዚህ ዓመት በ18 ወንድሞችና እህቶች ላይ የፈረደች ሲሆን ዘጠኙ ወንድሞች የተለያየ ርዝመት ያለው እስር ተበይኖባቸዋል። ከ40 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ያለፍርድ ታስረዋል፤ 19ኙ ደግሞ በቁም እስር ላይ ናቸው። በመላዋ ሩሲያ ወደ 300 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች በእምነታቸው ምክንያት ክስ ተመሥርቶባቸዋል።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የሚደርሰው ስደት ቢያሳዝነንም እንዲህ ያለው ፈተና መድረሱ አያስገርመንም። ይሖዋ ስደት እንደሚደርስብን አስቀድሞ ነግሮናል፤ ሆኖም ምንጊዜም የእሱ ድጋፍ እንደማይለየን ቃል ገብቶልናል። “የክብር መንፈስ ይኸውም የአምላክ መንፈስ” በሩሲያ ወንድሞቻችን ላይ እንዲያርፍ እንጸልያለን።—1 ጴጥሮስ 4:12-14