በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አሌክሳንደር ሽቼርቢና

ሚያዝያ 6, 2021
ሩሲያ

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም አሌክሳንደር ሽቼርቢና ላይ የሦስት ዓመት እስራት በየነ

የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም አሌክሳንደር ሽቼርቢና ላይ የሦስት ዓመት እስራት በየነ

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በወንድም አሌክሳንደር ሽቼርቢና ላይ የተላለፈው የእስር ቅጣት እንዲቀነስ አደረገ

ሰኔ 24, 2021 የክራስኖዳር ክልል አውራጃ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት በወንድም አሌክሳንደር ሽቼርቢና ላይ የተላለፈው ውሳኔ ትክክል ነው የሚል ብይን አስተላልፏል፤ ሆኖም በወንድም አሌክሳንደር ላይ መጀመሪያ የተላለፈበትን የሦስት ዓመት እስራት ወደ ሁለት ዓመት እስራት ለውጦለታል።

የፍርድ ውሳኔ

በክራስኖዳር ክልል የሚገኘው የአብንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ሚያዝያ 6, 2021 በወንድም አሌክሳንደር ሽቼርቢና ላይ የሦስት ዓመት እስራት ፈርዶበታል። ወንድም አሌክሳንደር ከፍርድ ቤት በቀጥታ ወደ እስር ቤት ተወስዷል። ወንድም አሌክሳንደር ውሳኔውን አስመልክቶ ይግባኝ ይጠይቃል።

አጭር መግለጫ

አሌክሳንደር ሽቼርቢና

  • የትውልድ ዘመን፦ 1976 (ሆልምስካያ፣ ክራስኖዳር ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ሁለቱንም ወላጆቹን በሞት አጥቷል። የከባድ መኪና ሾፌር፣ የመኪና ሜካኒክ እንዲሁም አናጺ ሆኖ ሠርቷል

  • ወጣት እያለ ቅርጫት ኳስ እና እግር ኳስ መጫወት ይወድ ነበር። በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ካጠና በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን አመነ። በ1999 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

በክራስኖዳር ክልል የሚገኙ ባለሥልጣናት የወንድም አሌክሳንደር ሽቼርቢናን ቤት ሁለት ጊዜ ማለትም ሚያዝያ እና ታኅሣሥ 2020 በረበሩ። በሁለቱም ጊዜያት አሌክሳንደር ለጥያቄ ወደ ጣቢያ ተወስዶ ነበር፤ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቹ ተወርሰውበታል።

የአሌክሳንደር ክስ በአብንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት መታየት የጀመረው መጋቢት 17, 2021 ነበር። በዚያ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ ሌሎች ወንድሞቻችን ሁሉ የአሌክሳንደር የፍርድ ሂደትም የተከናወነው በችኮላ ነው።

አሌክሳንደር ለፍርድ ቤቱ በድፍረት እንዲህ ብሏል፦ “እንደ እውነቱ ከሆነ የተከሰስኩት በአምላክ በማመኔ እና የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ነው፤ በሌላ አባባል በሩሲያ ፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 28 ላይ የተሰጠኝን መብት በመጠቀሜ ነው። ሃይማኖታዊ አመለካከቴ የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው፤ በመሆኑም ከጽንፈኝነት ጨርሶ የራቀ ነው።”

በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ድፍረትና እምነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ በመሆናቸው ይሖዋን እናመሰግነዋለን። “የአምላክን ፈቃድ” በመፈጸም መጽናታቸው የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያስገኝላቸው እንተማመናለን።—ዕብራውያን 10:36