ጥር 22, 2021
ሩሲያ
የሩሲያ ፍርድ ቤት እህት አናስታሲያ ስይቸቫ በስብሰባዎች ላይ በመገኘቷ ምክንያት ጥፋተኛ ናት ብሎ ፈረደባት
የፍርድ ውሳኔ
ሩሲያ ውስጥ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የኦብሉቸንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ጥር 21, 2021 እህት አናስታሲያ ስይቸቫ ጥፋተኛ ናት የሚል ፍርድ አስተላልፏል። እህት አናስታሲያ የሁለት ዓመት የገደብ እስር ተፈርዶባታል። እርግጥ እስር ቤት ገብታ አትታሰርም።
አጭር መግለጫ
አናስታሲያ ስይቸቫ
የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ቴፕሎዝዮርስክ፣ የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል)
ግለ ታሪክ፦ አራት ወንድሞችና እህቶች ነበሯት፤ ሆኖም ሁለቱ አሁን በሕይወት የሉም። ከሕክምና ኮሌጅ የነርሲንግ ዲግሪ አላት። በጥርስ ክሊኒክ ውስጥ ትሠራ ነበር፤ ከዚያም በሥነ አእምሮ ሆስፒታል ውስጥ ሠርታለች። ታላቅ እህቷ ከሞተች በኋላ የእህቷን ሁለት ልጆች ማሳደግ ጀመረች። እናቷም እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ለረጅም ጊዜ አስታማቸዋለች
በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለች ሕይወት አጭር መሆኑ ያሳስባት ነበር። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምር አነሳሳት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለጥያቄዎቿ አሳማኝ መልስ አገኘች። በ1994 ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች
የክሱ ሂደት
የሩሲያ ባለሥልጣናት ጥቅምት 2019 አናስታሲያን “ጽንፈኛ” በሚሏቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ከተቷት። በቢሮቢድዣን የሚገኘው የሩሲያ የፌዴራል ደህንነት ቢሮ የምርመራ ክፍል መስከረም 25, 2019 በአናስታሲያ ላይ የወንጀል ክስ መሠረተባት። የተከሰሰችው በይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ስብሰባ ላይ በመካፈሏ እና ስለ እምነቷ ለሌሎች በመናገሯ ምክንያት ነው።
በፍርድ ቤት ክሱ በተሰማበት ወቅት አቃቤ ሕጉ አናስታሲያ በስልክ ስታወራ እንዲሁም ስብሰባ ላይ ስትገኝ የተቀረጹ የድምፅና የቪዲዮ ቅጂዎችን አጫውቶ ነበር። አቃቤ ሕጉ እነዚህ ቅጂዎች እህታችን “በጽንፈኝነት” ድርጊት እንደተካፈለች የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንደሆኑ ገለጸ። አናስታሲያ፣ አቃቤ ሕጉ ማስረጃ ብሎ ያቀረባቸውን ነገሮች ተጠቅማ ምሥክርነት ሰጠች። በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ሰዎች ርኅራኄን፣ ምሕረትን፣ ትዕግሥትንና ሌሎች ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ እንደሚማሩ ገለጸች።
አናስታሲያ በፍርድ ቤቱ ፊት የመጨረሻ ቃሏን በሰጠችበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወቷ የጠቀማት እንዴት እንደሆነ አብራርታለች። ንግግሯ በከፊል ይህን ይመስላል፦ “ዛሬ ፍርድ ቤት የቆምኩት በእምነቴና በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈሌ የተነሳ ነው፤ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን በማንበቤ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመነጋገር ከጓደኞቼ ጋር በመሰብሰቤ፣ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር በመዘመሬና ወደ እሱ በመጸለዬ ነው።
“በዕብራውያን ምዕራፍ 10 ቁጥር 24 እና 25 ላይ የተሰጠውን ትእዛዝ እንዴት ችላ እላለሁ? ጥቅሱ ‘እንዲሁም እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ’ ይላል። ሉዓላዊው አምላክ ይሖዋ ራሱ ከክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር እንድሰበሰብ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳነብ፣ ሌሎችን እንዳበረታታና ለሌሎች ደግነት እንዳሳይ ካዘዘኝ እንዴት የእሱን ትእዛዝ እጥሳለሁ? እሱ እኮ ከልቤ የምወደው፣ የማከብረውና የማመልከው አምላኬ ነው።”
አናስታሲያ በድፍረት ለእምነቷ ጥብቅና መቆሟን እንዲሁም አዎንታዊና ልበ ሙሉ መሆኗን በመስማታችን በጣም ተደስተናል። ደስታዋን ይዛ መቀጠል እንድትችል እንዲሁም ይህ የእምነት ፈተና ጽናቷን ይበልጥ እንዲያጠነክረው እንጸልያለን።—ያዕቆብ 1:2, 3