በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኒኮላይ ኩዚችኪን (በስተ ግራ) እና ወንድም ቭያችስላቭ ፖፖቭ (በስተ ቀኝ)

ታኅሣሥ 18, 2020
ሩሲያ

የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም ኒኮላይ ኩዚችኪን እና ወንድም ቭያችስላቭ ፖፖቭ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላለፈ

የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም ኒኮላይ ኩዚችኪን እና ወንድም ቭያችስላቭ ፖፖቭ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላለፈ

የፍርድ ውሳኔ

ታኅሣሥ 18, 2020 በሶቺ የሚገኘው የኮሆስቲንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ኒኮላይ ኩዚችኪን እና ወንድም ቭያችስላቭ ፖፖቭ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ውሳኔ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ ወንድም ኒኮላይ አንድ ዓመት ከአንድ ወር፣ ወንድም ቭያችስላቭ ደግሞ አንድ ዓመት ከአሥር ወር እንዲታሰሩ ፈርዶባቸዋል። ሆኖም ፍርድ ከመተላለፉ በፊት ታስረው የቆዩበት ጊዜ ስለሚታሰብ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰዋል ማለት ይቻላል። ወንድም ቭያችስላቭ አሁንም በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ሲሆን ይለቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ወንድም ኒኮላይ ደግሞ ከቁም እስረኝነት ነፃ ተደርጓል።

አጭር መግለጫ

ኒኮላይ ኩዚችኪን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1951 (ኮስትሮማ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከተማረ በኋላ የፒያኖ ባለሙያ ሆኖ መሥራት ጀመረ። ከባለቤቱ ከኦልጋ ጋር ሦስት ወንዶች ልጆችን አሳድገዋል። የተዋጣለት የንብ እርባታ ባለሙያም ነው

    በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ ማየቱ በ1993 ራሱን ወስኖ እንዲጠመቅ አነሳስቶታል

ቭያችስላቭ ፖፖቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1974 (ቶምስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ከልጅነቱ ጀምሮ ሰዓሊ የነበረ ሲሆን ቤትን በማስዋብ ሙያ ተሰማርቷል። ከባለቤቱ ከዩሊያ ጋር የተገናኙት ኮሌጅ እያሉ ነው። በ1998 ትዳር ከመሠረቱ በኋላ አንድ ሴትና ሁለት ወንዶች ልጆች ወልደዋል። በ2010 ወደ ሶቺ ተዛወሩ። ቤተሰቡ የበረዶ ላይ ሸርተቴ ጨዋታና በባሕር ዳርቻዎች መንሸራሸር ይወዳሉ

    ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረችው ዩሊያ ነበረች። ቭያችስላቭ አባቱ ከሞቱ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አጽናንቶታል። በ2004 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

ጥቅምት 10, 2019 ምሽት ውሾችን የያዙና የታጠቁ የደህንነት ቢሮ ሠራተኞች በሶቺ፣ ሩሲያ የሚገኙ 36 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ፍተሻ አካሄዱ።

በቤቶቹ ላይ ፍተሻ ሲካሄድ ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች መሬት ላይ ተደፍተው እንዲተኙ ተደርጓል። ሞባይል ስልኮቻቸውን፣ ታብሌቶቻቸውን፣ ኮምፒውተሮቻቸውን፣ ጽሑፎቻቸውንና ማስታወሻ ደብተሮቻቸውን አልፎ ተርፎም ፖስት ካርዶቻቸውን ወስደውባቸዋል። የደህንነት ሠራተኞቹ አንዳንዶቹ ቤቶች ውስጥ የታገዱ ጽሑፎችን ሆን ብለው ደብቀው ነበር። ይህን ምክንያት በማድረግ ወንድም ኒኮላይ ኩዚችኪንን እና ወንድም ቭያችስላቭ ፖፖቭን ያዟቸው። በማግስቱ ሁለቱም ወንድሞች ችሎት ፊት ሳይቀርቡ እንዲታሰሩ ተደረገ።

ወንድም ኒኮላይ የተለያዩ ከባድ የጤና ችግሮች አሉበት። ሕክምና ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም የፍርድ ቤት ባለሥልጣናት “አንድን ሰው ከእስር ነፃ እንዲሆን ሊያደርጉ የሚችሉ የበሽታ ዓይነቶች” እንደሌሉበት በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል። ኒኮላይ በርካታ እስረኞች ባሉበት ክፍል ውስጥ የታሰረ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ሲጋራ ያጨሳሉ፤ ይህ ደግሞ የጤንነቱ ሁኔታ እያሽቆለቆለ እንዲሄድ አድርጓል።

ኒኮላይ እስር ቤት ውስጥ ለሕይወቱ አስጊ የሆኑ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም “እስር ቤት እንደ ራጅ ነው፤ አንድ ክርስቲያን ጥሩ ባሕርያት ያሉት መሆን አለመሆኑን በግልጽ ያሳያል” ብሏል። ኒኮላይ ሰላማዊና ደግ ሰው ሲሆን በራሱ ላይ ከማተኮር ይልቅ በመንፈስ ጭንቀት የተዋጡና ራሳቸውን ለማጥፋት ያስቡ የነበሩ እስረኞችን ይረዳ ነበር።

ኒኮላይ ችሎት ፊት ሳይቀርብ በእስር ያሳለፋቸው ወራት ስድስት ጊዜ ከተራዘሙ በኋላ ሚያዝያ 22, 2020 ከእስር ቤት ወጥቶ የቁም እስረኛ እንዲሆን ተደረገ። መቆም እንኳ እስኪያዳግተው አቅሙ በጣም ተዳክሞ ነበር። ሕክምና እንዲያገኝ የተፈቀደለት ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው።

ወንድም ቭያችስላቭ ደግሞ ችሎት ፊት ሳይቀርብ በእስር ያሳለፋቸው ወራት አሥራ አራት ጊዜ በመራዘማቸው ከቤተሰቡ ጋር ከአንድ ዓመት በላይ ተለያይቶ ቆይቷል።

ኒኮላይና ቭያችስላቭ የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ ላሳዩት እምነትና ቆራጥነት ያለንን አድናቆት መግለጽ እንፈልጋለን። እነዚህ ወንድሞች በመዝሙር 16:8 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንገድ እንደሚኖሩ አሳይተዋል፤ ጥቅሱ “ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አደርገዋለሁ። እሱ በቀኜ ስላለ ፈጽሞ አልናወጥም” ይላል።