በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሩሲያ ፖሊሶች መሣሪያና መራጃ ይዘው በኒዥኒ ኖቭጎሮድ ወደሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤት ሲሄዱ፤ ሐምሌ 2019 በዚህች ከተማ 31 ቤቶች በዚህ መልኩ ተፈትሸዋል

ነሐሴ 7, 2019
ሩሲያ

የሩሲያ ፖሊሶች ከ600 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ

የሩሲያ ፖሊሶች ከ600 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ

የሩሲያ ፖሊሶች እና የፌደራል ደህንነቶች (FSB) በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ በ613 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ፍተሻ አካሂደዋል። ባለሥልጣናቱ ከጥር 2019 ወዲህ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 332 ቤቶችን ፈትሸዋል፤ በ2018 የተፈተሹ ቤቶች አጠቃላይ ቁጥር ግን 281 ነበር።

በተለይ ከጥቂት ወራት ወዲህ ባለሥልጣናቱ በወንድሞቻችን ላይ እያደረሱ ያለው ጥቃት እየጨመረ መጥቷል። በሰኔ ወር 71 ቤቶች፣ በሐምሌ ወር ደግሞ 68 ቤቶች ተፈትሸዋል። በ2018 በወር የሚፈተሹት ቤቶች አማካይ ቁጥር 23.4 የነበረ ከመሆኑ አንጻር ይህ ከፍተኛ ጭማሪ ነው።

የሩሲያ ፖሊሶች በኒዥኒ ኖቭጎሮድ የሚገኝን አንድ ቤት ለመፈተሽ ሲገቡ

አብዛኛውን ጊዜ ፍተሻ በሚካሄድበት ወቅት መሣሪያ የታጠቁና ፊታቸውን የሸፈኑ በርካታ ፖሊሶች ወደ አንድ ቤት ይመጣሉ። አንዳንድ ጊዜም ፖሊሶቹ አደገኛ ወንጀለኛ የሚይዙ ይመስል ቤት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሕፃናትንና አረጋውያንን ጨምሮ በይሖዋ ምሥክሮቹ ላይ መሣሪያ ይደግናሉ። በርካታ ባለሙያዎች የቤይለር ዩኒቨርሲቲ ጄ. ኤም. ዶውሰን ኢንስቲትዩት ኦቭ ቸርች ስቴት ስተዲስ የቀድሞ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ዴሪክ ዴቪስ ከሰጡት ሐሳብ ጋር የሚስማሙ መሆኑ አያስገርምም፤ ዶክተር ዴሪክ ዴቪስ “እንደ ‘ጽንፈኝነት’ ተደርጎ መታየት ያለበት ሩሲያ እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ባሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የምታደርሰው ከፍተኛ ስደት ነው” ብለው ነበር።

ፍተሻው ብቻ ሳይሆን በወንድሞቻችን ላይ የተመሠረቱ ክሶች ቁጥርም ጨምሯል። በአሁኑ ወቅት ሩሲያና ክራይሚያ ውስጥ ክስ የተመሠረተባቸው ወንድሞችና እህቶች ቁጥር 244 ደርሷል። ይህ አኃዝ በታኅሣሥ 2018 110 ከነበረበት ተነስቶ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። ክስ ከተመሠረተባቸው 244 ወንድሞችና እህቶች መካከል 39ኙ ታስረዋል፤ 27ቱ የቁም እስር ላይ ናቸው፤ ከ100 የሚበልጡት ደግሞ የተለያየ ዓይነት ገደብ ተጥሎባቸዋል።

የሩሲያ ባለሥልጣናት በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቢቀጥሉም ‘በእነዚህ መከራዎች አንናወጥም።’ ከዚህ ይልቅ የእምነት ባልንጀሮቻችን በታማኝነት እንደጸኑ መስማታችን ያበረታታናል። ይሖዋ እነሱን አስመልክቶ የምናቀርበውን ጸሎት ስለሚሰማን እናመሰግነዋለን፤ ወደፊትም መስማቱን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—1 ተሰሎንቄ 3:3, 7