መጋቢት 9, 2021
ሩሲያ
የሰባ ሦስት ዓመት አረጋዊት የሆኑ አንዲት እህት በእምነታቸው ምክንያት ሊፈረድባቸው ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
በቼልያቢንስክ የሚገኘው የሜተለርጂቼስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት የእህት ቫለንቲና ሱቮሮቫን ጉዳይ ተመልክቶ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል። a አቃቤ ሕጉ በእህት ቫለንቲና ላይ እንዲተላለፍ የሚፈልገውን ብይን ገና አላሳወቀም።
አጭር መግለጫ
ቫለንቲና ሱቮሮቫ
የትውልድ ዘመን፦ 1948 (ሶሮቭስኮዬ፣ ኩርጋን ክልል)
ግለ ታሪክ፦ ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት በቼልያቢንስክ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከ30 ዓመት በላይ በመምህርነት ሠርተዋል። አትክልት መንከባከብ፣ መደነስ እና ሙዚቃ ማዳመጥ ይወዳሉ
በ1973 ከቭላዲሚር ጋር ትዳር መሠረቱ። ልጃቸው ኢጎር ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በካንሰር ሕይወቱ አልፏል። በቅርቡ ደግሞ እናታቸውና እህታቸው በሞት አንቀላፍተዋል
የክሱ ሂደት
መጋቢት 26, 2019 መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች በቼልያቢንስክ እና በዬማንዥዬሊንስክ የሚገኙ ከ20 በላይ የወንድሞቻችንን ቤቶች ፈተሹ። አሁን 73 ዓመት የሆናቸው እህት ቫለንቲና ረጅም ሰዓት የወሰደ ምርመራ ከተካሄደባቸው በኋላ ታኅሣሥ 5, 2019 የወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፤ ለክሱ ምክንያት የሆነው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸው እና ስለ እምነታቸው ለሌሎች መናገራቸው ነው። እህት ቫለንቲና በአሁኑ ወቅት የጉዞ ገደብ ተጥሎባቸዋል። ወንድም ቭላዲሚርም በክርስቲያናዊ እምነታቸው ምክንያት የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል።
እህት ቫለንቲና ተኝተው እያሉ መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ቤታቸውን በበረበሩበት ወቅት የሆነውን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “መታጠብ፣ ፀጉራችንን ማበጠር ወይም ልብሳችንን መቀየር አልቻልንም። ቤታችንን ገለባብጠው እያንዳንዷን ሥርቻ ፈተሹ፤ መሳቢያዎቹን፣ የጌጣጌጥ ማስቀመጫዎቹን፣ የገንዘብ ቦርሳዎቹን እንዲሁም ኪሶችን በሙሉ አንድም ሳያስቀሩ በረበሩ። . . . ድስቶቹን ሌላው ቀርቶ መጋረጃዎቹን እና አልጋችንን ጭምር ፈተሹ፤ ምንም የቀራቸው ነገር አልነበረም።”
እህት ቫለንቲና በዕድሜ ከመግፋታቸውም ሌላ የጤና እክል ስላለባቸው ይህ ስደት ጤንነታቸውን ይበልጥ እንዳይጎዳው ፈርተው ነበር።
እህት ቫለንቲና መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው ማጥናታቸው በመንፈሳዊ እንዳጠናከራቸው ተናግረዋል። “የዕለቱን ጥቅስ ማንበቤ፣ ባነበብኩት ላይ ማሰላሰሌና ያነበብኩትን በሥራ ላይ ማዋሌ ያጋጠሙኝን ፈተናዎች እንድቋቋም ረድቶኛል” ብለዋል።
እህት ቫለንቲና ለስብሰባዎች መዘጋጀታቸውና ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸው እንዲሁም የግል ጥናትና የቤተሰብ አምልኮ ማድረጋቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይናገራሉ። “በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ፣ ተግባራዊ ላደርገው የምችለው አዲስ ትምህርት አገኛለሁ” ብለዋል። አክለውም ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረባቸው በእጅጉ እንደሚያጽናናቸው ተናግረዋል፤ “አምላክ ስለሚረዳኝ ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ” ብለዋል።
በተጨማሪም እህት ቫለንቲና እሳቸውም ሆነ ሌሎቻችን ልንዘነጋው የማይገባው ነገር ምን እንደሆነ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ማንኛውንም ነገር ልንፈራ አይገባም። ጽኑ እና በእምነት ብርቱ እንሁን፤ እንዲሁም ማቴዎስ 6:33ን እና 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን እናስታውስ።”
እህት ቫለንቲና እና ወንድም ቭላዲሚርን ጨምሮ በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችን በመዝሙር 64:10 ላይ ለሚገኘው ሐሳብ እውነተኝነት ማስረጃ ናቸው፤ ጥቅሱ “ጻድቅ ሰው በይሖዋ ሐሴት ያደርጋል፤ እሱንም መጠጊያው ያደርጋል፤ ቀና ልብ ያላቸውም ሁሉ ይደሰታሉ” ይላል።
a ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ።