በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ሊዩድሚላ ፖኖማሬንኮ

ሚያዝያ 15, 2021
ሩሲያ

የሰባ ዓመቷ እህት ሊዩድሚላ ፖኖማሬንኮ የተመሠረተባቸው ክስ አሁንም አልተቋጨም

የሰባ ዓመቷ እህት ሊዩድሚላ ፖኖማሬንኮ የተመሠረተባቸው ክስ አሁንም አልተቋጨም

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

በሮስቶቭ ኦን ዶን ከተማ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት በእህት ሊዩድሚላ ፖኖማሬንኮ ላይ ከተመሠረተው ክስ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ውሳኔውን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል። a

አጭር መግለጫ

ሊዩድሚላ ፖኖማሬንኮ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1950 (ኦላ፣ ማጋዳን ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት በአንድ ፋብሪካ ውስጥ የኤሌክትሪክ ባለሙያ ሆነው ሠርተዋል። ሁለት ሴት ልጆችና ሁለት የልጅ ልጆች አሏቸው። ማንበብና ጥልፍ መጥለፍ ያስደስታቸዋል። ከባድ የጤና ችግር ያለባቸውን ባለቤታቸውን ያስታምማሉ

  • መጽሐፍ ቅዱስን ሲማሩ ልባቸውን በጥልቅ የነካው የፈጣሪን የግል ስም ማወቃቸው ነው። አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ማወቃቸውም ትኩረታቸውን ስቦታል። በ1998 ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር ሆኑ

የክሱ ሂደት

ሰኔ 6, 2019 በእህት ሊዩድሚላ ፖኖማሬንኮ ላይ ክስ ተመሠረተባቸው። ከተመሠረተባቸው ክሶች መካከል “ጽንፈኛ” የሆነ ድርጅት ሃይማኖታዊ ስብሰባ የሚያደርግበት ቦታ መስጠት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ማካፈል ይገኙበታል።

እህት ሊዩድሚላ በሩሲያ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች የሚደርስባቸው ስደት እሳቸውም ላይ መድረሱ እንደማይቀር ጠብቀው ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “በሞስኮና በታጋንሮግ ባሉ ወንድሞችና እህቶች ላይ ስደት ማድረስ ሲጀምሩ ይዋል ይደር እንጂ ሁላችንም የዚህ ዕጣ ተካፋዮች መሆናችን እንደማይቀር ገብቶኝ ነበር።”

ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዘው በወጡት ገደቦች ምክንያት ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ፍርድ ቤት አብረዋቸው ተገኝተው ድጋፍና ማበረታቻ ሊሰጧቸው አልቻሉም። እህት ሊዩድሚላ ስለዚህ ሁኔታ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “ፍርድ ቤት ብቻዬን እንደምቀርብ ሳውቅ ፍርሃትና ጭንቀት ተሰምቶኝ ነበር፤ ስለዚህ ወደ ፍርድ ቤት ስሄድ የመንግሥቱን መዝሙሮች የማንጎራጎርና ወደ ይሖዋ የመጸለይ ልማድ አዳበርኩ። እንዲህ ማድረጌ ከፍተኛ ብርታት እንደሚሰጠኝ አስተውያለሁ። ፍርድ ቤት ስቀርብ ጭንቀት አይሰማኝም፤ ደግሞም ጊዜው ቶሎ ያልፍልኛል።”

በተጨማሪም እህት ሊዩድሚላ ይህ ሁኔታ የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑት ባለቤታቸውና በሁለት ሴት ልጆቻቸው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ክስ የቀረበብኝ ለምን እንደሆነ መረዳት ከብዷቸዋል። ሁኔታው በጤንነቴ ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያዩ በጣም ተጨንቀዋል።” አክለውም “በጊዜ ሂደት ቤተሰቦቼ [የቀረበብኝ ክስ] ምን ያህል መሠረተ ቢስ እንደሆነ ተገንዝበዋል፤ የእነሱ ድጋፍ መጽናት እንድችል ረድቶኛል” በማለት ተናግረዋል።

እህት ሊዩድሚላ ስደት የደረሰባቸው መሆኑ ቅንዓታቸውን አላቀዘቀዘውም። እንዲህ ብለዋል፦ “አሁን በእኔ ላይ እየደረሰ ያለውንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ወደፊት የሚከናወነውን ነገር በተመለከተ ምንም የምጨነቅበት ምክንያት ስለሌለ ልቤ በደስታ ተሞልቷል። ከይሖዋ ጋር ያለኝ ወዳጅነት ይበልጥ እየተጠናከረ ሄዷል። የማቀርበው ጸሎት ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኗል፤ አሁን የልቤን ሁሉ አውጥቼ ረዘም ላለ ጊዜ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ።”

እህት ፖኖማሬንኮ የይሖዋን መንፈስ እርዳታ ማግኘታቸውን እንደሚቀጥሉ እንዲሁም “ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ጥላ ሥር” መሆን የሚያስገኘውን በረከት እንደሚያጣጥሙ እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 91:1

a ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ።