በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ቭላዲሚር አሉሽኪን በቁጥጥር ሥር ውሎ ከመታሰሩ በፊት

ኅዳር 13, 2019
ሩሲያ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩሲያ ወንድም አሉሽኪንን እንድትለቅ ጥያቄ አቀረበ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩሲያ ወንድም አሉሽኪንን እንድትለቅ ጥያቄ አቀረበ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተ.መ.ድ.) አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድን (ዎርኪንግ ግሩፕ ኦን አርቢትራሪ ዲቴንሽን [WGAD]) ሩሲያ ወንድም ቭላዲሚር አሉሽኪንን አላግባብ በእስር ማቆየቷን የሚያወግዝ ባለ 12 ገጽ ሪፖርት አቅርቧል። ቡድኑ፣ ሩሲያ ወንድም አሉሽኪንን እንድትለቅ እንዲሁም ለተፈጸመበት የመብት ጥሰት ተገቢውን ካሳ እንድትከፍል በሪፖርቱ ላይ ጥያቄ አቅርቧል።

ሐምሌ 15, 2018 ጠመንጃ የታጠቁና ጭንብል ያጠለቁ ከአስር በላይ የሚሆኑ ፖሊሶች ኃይል ተጠቅመው ወደ ወንድም አሉሽኪን ቤት በመግባት በቁጥጥር ሥር አዋሉት። ፖሊሶቹ አራት ሰዓት ገደማ ለሚሆን ጊዜ የወንድም አሉሽኪንን ቤት ፈትሸው ተንቀሳቃሽ ስልኮችን፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን፣ መጽሐፍ ቅዱሶችን እና ሌሎች ጽሑፎችን ከወሰዱ በኋላ ወንድም አሉሽኪንን ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዘውት ሄዱ።

ወንድም ቭላዲሚር አሉሽኪን ጥር 2019 ላይ በፔንዛ ከተማ በሚገኘው የፒርቮማይስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ውስጥ ሆኖ

የአካባቢው ባለሥልጣናት ወንድም አሉሽኪንን በጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ ለሁለት ቀናት ካቆዩት በኋላ በፔንዛ ከተማ የሚገኘው የፒርቮማይስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት፣ ፍርድ የሚጠባበቁ ተከሳሾች ማቆያ እስር ቤት ውስጥ ለሁለት ወራት እንዲታሰር አዟል። ፍርድ ቤቱ ወንድም አሉሽኪን ያለፍርድ በእስር የሚቆይበትን ጊዜ ከአንዴም ሁለቴ እንዲራዘም አድርጓል። ወንድም አሉሽኪን ለስድስት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ያለፍርድ ከታሰረ በኋላ በቁም እስር እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን እስካሁንም ድረስ በዚህ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ወንድም አሉሽኪን ጥፋተኛ አለመሆኑ ታይቶ በነፃ እንዲለቀቅ፣ አግባብ ያልሆነ እስራትን ለሚያጣራው ቡድን (WGAD) ጥያቄ አቅርቧል። ለተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሚሠራው ይህ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ በፖሊስ እንደተያዙ፣ በፍርድ ቤት የቁም እስር እንደተፈረደባቸው፣ ያለፍርድ በእስር እንደቆዩ አሊያም አላግባብ እንደታሰሩ የሚናገሩ ሰዎች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች ይመረምራል።

አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድኑ (WGAD) ሩሲያ ወንድም አሉሽኪን ጽንፈኝነት በሚንጸባረቅባቸው እንቅስቃሴዎች ተሳትፏል በሚል የመሠረተችውን ክስ ከመረመረ በኋላ የሚከተለው ድምዳሜ ላይ ደርሷል፦ “አቶ አሉሽኪን የተሳተፉባቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሰላማዊ የሆኑ ሃይማኖታዊ ውይይቶች ነበሩ። አቶ አሉሽኪን በስምምነቱ [ሩሲያ አባል የሆነችበት ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት] አንቀጽ 18 ላይ የሚገኘውን የሃይማኖት ነፃነት መብታቸውን ከመጠቀም ውጭ ምንም ነገር እንዳላደረጉ ቡድኑ በግልጽ መመልከት ችሏል።” በመሆኑም በሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው “አጣሪ ቡድኑ አቶ አሉሽኪን በቁጥጥር ሥር መዋልም ሆነ ያለፍርድ መታሰር እንዳልነበረባቸውና ከዚህ በኋላም ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደማይገባ ያምናል።” በተጨማሪም አጣሪ ቡድኑ የሩሲያ መንግሥት “በአቶ አሉሽኪን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ኢፍትሐዊ ድርጊት ሳይውል ሳያድር እንዲያስተካክል” ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን “ይህን ኢፍትሐዊ ድርጊት ማስቆም የሚቻልበት ትክክለኛው መንገድ አቶ አሉሽኪንን በአፋጣኝ መልቀቅ እንደሆነ” አበክሮ ገልጿል።

አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድኑ ሩሲያ ውስጥ እንደ ወንድም አሉሽኪን ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው ሌሎች ሰዎች እንዳሉም አስተውሏል። ወንድም አሉሽኪን “በአሁኑ ጊዜ ሩሲያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ነፃነታቸውን [ማለትም በዓለም አቀፍ ሕግ የተከበረላቸውን መብት] በመጠቀማቸው ምክንያት ብቻ በቁጥጥር ሥር ከሚውሉ፣ ለእስር ከሚዳረጉና በወንጀል ከሚከሰሱ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ ብቻ ነው።” በመሆኑም አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድኑ በወንድም አሉሽኪን ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሩሲያ በሚገኙ ወንድሞቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ስደት ያወገዘ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከተው “ከአቶ አሉሽኪን ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ” የይሖዋ ምሥክሮችን በሙሉ እንደሆነ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።

የሩሲያ መንግሥት፣ አጣሪ ቡድኑ ላቀረበው ጥያቄ ገና ምላሽ አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ በፔንዛ የሚገኙ የሩሲያ ባለሥልጣናት ነሐሴ 2019 ላይ የወንድም አሉሽኪንን ጉዳይ ለፍርድ ቤት አቅርበውት ነበር። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ለኅዳር 15፣ 19 እና 22, 2019 ቀጠሮ ሰጥቷል።

የሩሲያ ፍርድ ቤት ከወንድም አሉሽኪን ጉዳይ ጋር በተያያዘ የመጨረሻውን ውሳኔ በሚያደርግበት ወቅት አጣሪ ቡድኑ ያቀረበውን ሪፖርት ከግምት እንደሚያስገባ ተስፋ ብናደርግም ሙሉ እምነታችንን የምንጥለው በይሖዋ ላይ ነው። በመሆኑም ልክ እንደ መዝሙራዊው “አልፈራም። . . . ይሖዋ ረዳቴ ሆኖ ከጎኔ አለ። . . . ይሖዋን መጠጊያ ማድረግ ይሻላል” እንላለን።—መዝሙር 118:6-9