ሚያዝያ 30, 2021
ሩሲያ
የአካል ጉዳተኛ የሆኑ የ73 ዓመት እህት በይሖዋ በመታመን በድፍረት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ነው
ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ
ግንቦት 25, 2021 የየፕሪሞርይስ ክልላዊ ፍርድ ቤት እህት ልዩድሚላ ሹት ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። መጀመሪያ ላይ የተላለፈባቸው ብይን በዚያው ይጸናል። እርግጥ በአሁኑ ወቅት ወህኒ አይወርዱም።
ግንቦት 19, 2021 በፕሪሞርይስ ክልል የሚገኘው የናደዠዲንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት የ73 ዓመት አረጋዊ የሆኑት እህት ልዩድሚላ ሹት ጥፋተኛ ናቸው የሚል ውሳኔ አስተላለፈ። እህት ልዩድሚላ የአራት ዓመት የገደብ እስር ተበይኖባቸዋል።
አጭር መግለጫ
ልዩድሚላ ሹት
የትውልድ ዘመን፦ 1947 (ማካሮቭ፣ ሳካሊን ደሴት)
ግለ ታሪክ፦ በ2000 መጀመሪያ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲማሩ ልባቸው በጥልቅ ተነካ። በ2003 ተጠመቁ። በዚያው ዓመት ባለቤታቸውን በሞት አጡ። ሦስት ልጆችና ሦስት የልጅ ልጆች አሏቸው። ከባድ የጤና ችግር ስላለባቸው ከሌሎች እርዳታ ውጭ ብቻቸውን መንቀሳቀስ አይችሉም
የክሱ ሂደት
ኅዳር 2017 ፖሊሶች በራዝዶኖዬ መንደር በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ክትትል ማድረግ ጀመሩ። የካቲት 2020 ፖሊሶቹ በእህት ልዩድሚላ ሹት ላይ ክስ መሠረቱባቸው። እህት ልዩድሚላ በዕድሜ የገፉና በግልጽ የሚታይ የአቅም ገደብ ያለባቸው ቢሆንም ፖሊሶቹ ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይሄዱ ገደብ ጥለውባቸዋል።
የክስ ሂደቱ በእህት ልዩድሚላ ላይ ተጨማሪ አካላዊና ስሜታዊ ጫና አስከትሎባቸዋል። የማየት ችሎታቸው እያሽቆለቆለ ከመሄዱ የተነሳ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ በተጨማሪም ለእንቅልፍ እጦት ተዳርገዋል። ያም ሆኖ እህት ልዩድሚላ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመናቸው እሱ ጥበቃ እያደረገላቸው እንዳለ እርግጠኛ ናቸው። በኢሳይያስ 26:3 ላይ ቃል በገባው መሠረት “ዘላቂ ሰላም” እየሰጣቸው ነው።
ወንድሞችና እህቶችም ለእህት ልዩድሚላ ፍቅራዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው። በተለይ ወንድሞች ስለ እሳቸው እንደሚጸልዩላቸው ማወቃቸው በጣም ያስደስታቸዋል። “ይህን ፈጽሞ አልረሳውም” በማለት ተናግረዋል።
ወንድ ልጃቸውና የመጨረሻዋ ሴት ልጃቸው የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ከጎናቸው በመሆን ድጋፍ አድርገውላቸዋል።
እህት ልዩድሚላ የፍርድ ውሳኔያቸውን እየተጠባበቁ ባሉበት በዚህ ወቅት “በአምላክ ኃይል” እንደሚታመኑ እርግጠኛ በመሆን ስለ እሳቸው መጸለያችንን እንቀጥላለን።—2 ጢሞቴዎስ 1:8