በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች መፈጸማቸውን የሚከታተለው የአውሮፓ ምክር ቤት የሚኒስትሮች ኮሚቴ

ታኅሣሥ 21, 2022
ሩሲያ

የአውሮፓ ምክር ቤት ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ በጥብቅ አሳሰበ

የአውሮፓ ምክር ቤት ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ በጥብቅ አሳሰበ

የአውሮፓ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ታኅሣሥ 9, 2022 ለሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ ላይ ሩሲያ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በቅርቡ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች እንድታከብር አሳሰቡ። ከእነዚህ ውሳኔዎች መካከል ሰኔ 2022 የተላለፈው ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የጣለችው እገዳ ሕጋዊ እንዳልሆነ የሚገልጸው ታሪካዊ ውሳኔ ይገኝበታል። a

እንደሚታወቀው፣ ሩሲያ ከመጋቢት 2022 አንስቶ ከአውሮፓ ምክር ቤት አባልነት ወጥታለች፤ ያም ቢሆን የሩሲያ መንግሥት፣ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከመስከረም 16, 2022 በፊት ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች የመተግበር ግዴታ እንዳለበት ደብዳቤው አሳስቧል። በተጨማሪም የአውሮፓ ምክር ቤት የሚኒስትሮች ኮሚቴ፣ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ሩሲያ ውስጥ ያላቸውን ተፈጻሚነት መከታተሉን ይቀጥላል።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሰኔ 2022 ፍርድ ካስተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ኮሚቴው፣ የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2017 በይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ላይ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ የሩሲያን መንግሥት በጥብቅ ሲያሳስብ ቆይቷል። በተጨማሪም ኮሚቴው ሩሲያ “የይሖዋ ምሥክሮችን ድርጅት ጽንፈኛ ብሎ ለመፈረጅ መሠረት የሆነውን የፀረ ጽንፈኝነት ሕግ እንድታርም . . . ፣ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተከፈቱ የወንጀል ክሶችን እንድታቋርጥና የታሰሩትን እንድትፈታ፣ የተላለፈባቸውን የጥፋተኝነት ብይን ሙሉ በሙሉ እንድትሰርዝ እንዲሁም የተያዙባቸው ንብረቶች እንዲመለሱ ወይም ካሣ እንዲከፈላቸው” ጥሪ አቅርቧል። b

እስካሁን ድረስ በእገዳው ምክንያት ከ660 በላይ የሚሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሕግ ተጠያቂ ሆነዋል፤ እምነታቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማራመዳቸው ምክንያት ብቻ። ከእነዚህም መካከል ከ360 በላይ የሚሆኑት ለተወሰነ ጊዜ ታስረዋል፣ 114 የሚሆኑት ደግሞ አሁንም እስር ቤት ወይም ማረፊያ ቤት ናቸው።

ከ450 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች በሩሲያ የጽንፈኞችና የአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል፤ ይህ ደግሞ በእነሱ አልፎም በቤተሰቦቻቸው ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ ነው። ማንኛውም ሰው ሊያገኘው በሚችለው በዚህ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉ ማኅበረሰቡ እንዲያገልላቸውና ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው አድርጓል። ተጨማሪ ችግሮችም እየደረሱባቸው ነው፤ ለምሳሌ፣ የባንክ ሒሳባቸው ታግዷል፣ ኢንሹራንስ መግባትም ሆነ የገቡትን ማደስ፣ ንብረት መሸጥ፣ በንግድ እንቅስቃሴዎች መካፈል፣ ውርስ መቀበል ሌላው ቀርቶ የሞባይል ሲም ካርድ መግዛት እንኳ ከባድ ሆኖባቸዋል።

ደስ የሚለው፣ የአውሮፓ ምክር ቤት በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍትሕ እንዲያገኙ ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል። እስከዚያው ግን የሩሲያ ወንድሞቻችን በምን ሁኔታ እንዳሉ በማወቅ በእጅጉ እንበረታታለን፤ በእምነት፣ በድፍረትና በደስታ እየጸኑ እንደሆነ የሚገልጹ ሪፖርቶች jw.org ላይ በየጊዜው ይወጡልናል። ይህም ለመላው የወንድማማች ማኅበር የብርታት ምንጭ ሆኗል፤ ለዚህም ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—ፊልጵስዩስ 1:12-14

a የሞስኮ የይሖዋ ምሥክሮችና ሌሎች (ማመልከቻ ቁ. 302/02) እንዲሁም ክሩፕኮና ሌሎች (ማመልከቻ ቁ. 26587/07) እና የሩሲያ ፌዴሬሽን በሚለው የክስ መዝገብ ላይ አንቀጽ ሦስትን እና አምስትን ተመልከት።

b የሞስኮ የይሖዋ ምሥክሮችና ሌሎች (ማመልከቻ ቁ. 302/02) እንዲሁም ክሩፕኮና ሌሎች (ማመልከቻ ቁ. 26587/07) እና የሩሲያ ፌዴሬሽን በሚለው የክስ መዝገብ ላይ አንቀጽ አራትን ተመልከት።