ግንቦት 1, 2020
ሩሲያ
የአውሮፓ ባለሥልጣናት በሩሲያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰውን ስደት አወገዙ
መጋቢት 12, 2020 ከ30 የሚበልጡ የአውሮፓ አገራት ሩሲያ በወንድሞቻችን ላይ የምታደርሰውን ስደትና ሥቃይ አጥብቀው አውግዘዋል። እነዚህ ባለሥልጣናት ሩሲያን ያወገዙት የአውሮፓ ደህንነትና ትብብር ድርጅት ቋሚ ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ላይ ነበር። ከምክር ቤቱ ኃላፊነቶች መካከል ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር ይገኝበታል።
የአውሮፓ ኅብረት አባል የሆኑ 27 አገራትና ሌሎች 6 አገራት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የሚከተለውን የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፦ “የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታ እያሳሰበው ነው፤ ምክንያቱም የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸው እየተበረበረ፣ ያለአግባብ እየታሰሩ፣ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደባቸው፣ እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ እስር እየተበየነባቸው እንዲሁም በሌሎች መንገዶች የጥቃት ዒላማ እየሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተይዘው ሲወሰዱ ወይም እስር ቤት ከገቡ በኋላ በእስር ቤት ጠባቂዎች አሊያም በፖሊሶች ከፍተኛ ሥቃይና በደል እንደደረሰባቸው የሚገልጹ ዘገባዎችን በመስማታችን በእጅጉ አዝነናል።”
በምክር ቤቱ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር የሆኑት ኒል ቡሽ በምክር ቤቱ ፊት ባቀረቡት ንግግር ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሐምሌ 2017 የይሖዋ ምሥክሮች ‘ጽንፈኛ’ ተብለው እንዲፈረጁ የተደረገውን ውሳኔ ለመቀልበስ የቀረበውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ያስተላለፈው ብይን 175,000 የሩሲያ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርቡት አምልኮ እንደ ወንጀል እንዲቆጠር ከማድረጉም ሌላ በሩሲያ ሕገ መንግሥትም ሆነ በተለያዩ የምክር ቤቱ ድንጋጌዎች ላይ የሰፈረውን የሃይማኖት ነፃነት መብት የሚጻረር ነው።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ብይን ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶ በመላው ሩሲያ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰው እስር፣ የወንጀል ምርመራና ስደት ጨምሯል። እኛም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እየደረሰ ስላለው ሥቃይና በደል የሰማነው ዘገባ በጣም እንዳሳሰበን መግለጽ እንፈልጋለን።”
የአውሮፓ ባለሥልጣናት ከጠቀሷቸው ዘገባዎች መካከል አንዱ አምስት የይሖዋ ምሥክሮች የካቲት 6, 2020 ስለደረሰባቸው ድብደባ የሚገልጸው ዘገባ ነው። በሩሲያ የሚገኝ አንድ እስር ቤት ጠባቂዎች አሌክሲ ቡደንቹክ፣ ጀናዲ ጀርመን፣ ሮማን ግሪዳሶቭ፣ ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ እና አሌክሲ ሚረትስኪ የተባሉ አምስት ወንድሞቻችንን ክፉኛ ደብድበዋቸዋል። የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ እንደዘገበው “ሁሉም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አንደኛው [ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ] ሆስፒታል ገብቶ መታከም አስፈልጎታል። . . . በተጨማሪም ቫዲም ኩትሰንኮ የካቲት 10, 2020 ከመታሰሩ በፊት ከፍተኛ ሥቃይ እንደደረሰበት ተናግሯል፤ ፖሊሶች ስለ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች መረጃ እንዲሰጣቸው ለማስገደድ ሲሉ በተደጋጋሚ እንደደበደቡትና እንዳነቁት እንዲሁም በኤሌክትሪክ በመንዘር እንዳሠቃዩት ገልጿል።”
ከዚህም ሌላ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ እንዲህ ብሏል፦ “ሥቃይና እንግልት ማድረስ ዘግናኝ ከሆኑ የሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊ ክብር ጥሰቶች መካከል ይመደባሉ። ሰዎችን ማሠቃየት ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነትን፣ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣውን ሥቃይን እንዲሁም ሌሎችን የጭካኔ፣ አረመኔና አዋራጅ ድርጊቶችና ቅጣቶች የሚያወግዝ ድንጋጌ ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ይጥሳል፤ የሩሲያ ፌዴሬሽን ደግሞ ሁሉንም ድንጋጌዎች ተቀብላለች።”
በተጨማሪም የአውሮፓ መሪዎች ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የምታደርሰው ስደት የሩሲያ ፌዴሬሽን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአገሪቱ ውስጥ በነፃነት ሃይማኖታቸውን ማራመድ እንደሚችሉ ከዚህ ቀደም ለምክር ቤቱ ከሰጠችው ዋስትና ጋር በቀጥታ እንደሚቃረን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ እንዲህ ብሏል፦ “የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሚያዝያ 20, 2017 የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር ማዕከልና ሌሎች ድርጅቶች ‘ጽንፈኛ’ እንደሆኑ በመግለጽ እገዳ ጥሎባቸዋል። ይህ ከሆነ በኋላም የሩሲያ መንግሥት ልዑካን የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም ሆነ ወደፊት ሃይማኖታቸውን በነፃነት ማራመድ እንደሚችሉ እንዲሁም የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት እንደማይነፈጋቸው በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ያም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸው እንደተበረበረ፣ ያለአግባብ እንደታሰሩ እንዲሁም የወንጀል ምርመራ እንደተደረገባቸው የሚገልጹ በርካታ ሪፖርቶችን እየሰማን ነው።”
የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች እንደገለጹት “በሩሲያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅቶች በሙሉ ከታገዱ ወዲህ 869 ቤቶች እንደተበረበሩ፣ 26 ሰዎች ፍርድ ሳይበየንባቸው እንደታሰሩ፣ 23 ሰዎች በቁም እስር ላይ እንዳሉ፣ 316 ሰዎች ክስ እንደተመሠረተባቸው እንዲሁም 29 ሰዎች እንደተፈረደባቸው ሪፖርት ተደርጓል።”
አምባሳደር ቡሽ እንዲህ ብለዋል፦ “ከላይ ያሉት አኃዞች በግልጽ እንደሚያሳዩት የይሖዋ ምሥክሮች በየትኛውም መንገድ እምነታቸውን መግለጻቸው ቤታቸው እንዲበረበር፣ ረዘም ላለ ጊዜ ያለፍርድ እንዲታሰሩ፣ ክስ እንዲመሠረትባቸው እንዲሁም እስር እንዲበየንባቸው ሊያደርግ ይችላል። ቤቶቹ የሚበረበሩበት መንገድ እንዲሁም በአንድ ከተማ ውስጥ ያሉ በርካታ ቤቶች በተመሳሳይ ቀን የሚበረበሩ መሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የተደራጀ ጥቃት እየደረሰባቸው እንዳለ ያሳያል።”
ስለ ሃይማኖት ነፃነት የሚያጠኑ ባለሙያዎችም በሩሲያ ባሉ ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰውን እንግልት አውግዘዋል። ጠበቃ፣ ፖለቲከኛና የሮም ካቶሊክ የሥነ መለኮት ምሁር የሆኑት ኦስትሪያዊቷ ዶክተር ጉድሩን ኩግለር የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ሚያዝያ 2017 ሩሲያ ውስጥ ከታገዱ ወዲህ ሁኔታው በጣም እየከፋ ሄዷል። . . . በሩሲያ ፍርድ የተበየነባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ ፍርድ የተላለፈባቸው በፀረ ጽንፈኝነት ሕግ መሠረት ነው፤ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይህ ሕግ ‘ግልጽ እንዳልሆነና ከልክ በላይ ለትርጉም ክፍት’ እንደሆነ ገልጸዋል። በአንቀጽ 282.2 መሠረት አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች አባል መሆኑና በግለሰብ ደረጃ አምልኮ መፈጸሙ በራሱ እስር እንዲበየንበት የሚያደርግ ወንጀል ነው። . . . ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮችና ብዙ አባል በሌላቸው ሌሎች ሃይማኖቶች ላይ የምታደርሰውን ስደት ማቆም አለባት!”
የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ እንደገለጸው ሩሲያን ጨምሮ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት “በሰዎች ላይ የሚደርስን እንግልት የመከላከል፣ እንዲህ ዓይነት ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ለፍርድ የማቅረብ እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የመለየትና ካሳ እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በመሆኑም የሩሲያ ፌዴሬሽን እንዲህ ያሉ ድርጊቶች እንደደረሱ የሚገልጹ ሪፖርቶችን በሙሉ በአፋጣኝና በተሟላ ሁኔታ በማጣራት የድርጊቱ ተካፋዮች በሙሉ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እንድታደርግ እንጠይቃለን። . . . በተጨማሪም ሰብዓዊ መብታቸው የሆነውን ነገር በማድረጋቸው ብቻ ያለአግባብ ክስ ከተመሠረተባቸውና ከታሰሩት ሰዎች ጋር በተያያዘ ባለሥልጣናት ሁሉንም ክሶች እንዲያቋርጡ ጥሪ እናቀርባለን። ከዚህም ሌላ የሩሲያ ፌዴሬሽን ሐሳብን የመግለጽ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመሰብሰብ እንዲሁም የሃይማኖትና የእምነት ነፃነትን በማክበር፣ የአናሳ ቡድኖች አባላትን መብት በማስጠበቅ እንዲሁም ሁሉም ሰው ፍትሐዊ ፍርድ እንዲያገኝ በማድረግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን እንድታከብር እንጠይቃለን።”
ሩሲያ ሃይማኖታዊ ነፃነትን በማክበር ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ምላሽ ሰጠችም አልሰጠች ይሖዋ በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እውነተኛ ፍትሕ እስኪሰፍንላቸው ድረስ በትዕግሥትና በድፍረት እንዲጸኑ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 10:18