በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጋቢት 7, 2022
ሩሲያ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሩሲያ የይሖዋ ምሥክሮችን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች እንደጣሰች ገለጸ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሩሲያ የይሖዋ ምሥክሮችን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች እንደጣሰች ገለጸ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት (ECHR) የካቲት 22, 2022 ባሳለፋቸው ሁለት ውሳኔዎች ላይ ለ15 የይሖዋ ምሥክሮች ፈርዷል። ውሳኔ የተላለፈባቸው ክሶች ከ2010 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ሕግ አስከባሪ አካላት የወንድሞቻችንን ቤቶች በበረበሩበት ወቅት በእነሱ ላይ ካደረሱት በደል ጋር የተያያዙ ናቸው። ውሳኔው ሩሲያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያላቸውን መሠረታዊ መብት ማለትም የሃይማኖት ነፃነታቸውን እንደጣሰች ይገልጻል። ሩሲያ በድምሩ ከ99,000 ዩሮ በላይ (112,323 የአሜሪካ ዶላር) ካሳ እንድትከፍል ታዝዛለች። ውሳኔው የመጨረሻ ሲሆን ከዚህ በኋላ ይግባኝ መጠየቅ አይቻልም።

ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ውሳኔዎች ያስተላለፈው በሩሲያ ላይ የተመሠረቱ ስድስት ክሶችን ተመልክቶ ነው። a ክሶቹ በሩሲያ ባለሥልጣናት ላይ የተመሠረቱት ‘ሕጋዊ የፍተሻ ፈቃድ ሳይኖራቸው በርካታ የግል ቤቶችንና አንድን የስብሰባ አዳራሽ በርብረዋል፤ በመስበካቸው ምክንያት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሁለት እህቶችን ልብሳቸውን አስወልቀው ፈትሸዋል እንዲሁም የግል ንብረቶችን ወርሰዋል’ በሚል ነው። በአንዳንዶቹ ጊዜያት ብርበራው የተካሄደው ጭምብል ባጠለቁና መሣሪያ በታጠቁ የፌዴራል ደህንነት አባላት ሲሆን እነዚህ ፖሊሶች በወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ጉልበት ተጠቅመዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች የሕግ ቡድን፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ የሆኑትን አንድሬ ካርቦኖን አማክሮ ነበር። ጠበቃው እነዚህ ውሳኔዎች ስላላቸው ጥቅም ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “[ውሳኔዎቹ] ሩሲያ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፍትሐዊና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ስትፈትሽ እንደቆየች ለማረጋገጥ መሠረት ይሆናሉ፤ ይህም የይሖዋ ምሥክሮች በ2017 ከታገዱበት ጊዜ አንስቶ የተካሄዱትን 1,700 ፍተሻዎች ያካትታል። ከዚህ በኋላ አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ብቻ ቤቱ ከተፈተሸ ይህ ሁኔታ ሕገ ወጥና የአውሮፓን ስምምነት እንደጣሰ ተደርጎ ይቆጠራል።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ፍርድ ቤቱ፣ የሩሲያ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እንዳይሰብኩ መከልከላቸውን ማውገዙ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ስብከትን ባለሥልጣናቱ ጣልቃ ሊገቡበት የማይገባ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ አድርጎ እንደሚመለከተው ያሳያል።”

በእርግጥ እነዚህ ሁለት ውሳኔዎች በአሁኑ ወቅት በሩሲያ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ለሚደርሰው ጭቆና መፍትሔ አይሰጡም፤ ሆኖም ወደፊት በድርጅታችን ላይ ከተጣለው እገዳ ጋር በተያያዘ ለሚደረጉ ውሳኔዎች መሠረት ይሆናሉ። በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ገና ያልታዩ የሩሲያ የይሖዋ ምሥክሮች ያቀረቧቸው ሌሎች 60 አቤቱታዎች አሉ። ከእነዚህ ሁለት ውሳኔዎች በመነሳት ፍርድ ቤቱ ከሌሎቹ አቤቱታዎች ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ ብይን ያስተላልፋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

የሰብዓዊ መብቶች ባለሥልጣናት በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለሚያሳዩት የማይናወጥ ታማኝነት እውቅና በመስጠታቸው ሁላችንም ተደስተናል። እነዚህ ውሳኔዎች ይሖዋ ለስሙ በታማኝነት ጥብቅና ለመቆምና ሉዓላዊነቱን ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት እየባረከው እንዳለ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።—መዝሙር 26:11

a ስድስቱ ክሶች የሚከተሉት ናቸው፦ ከሳሽ ቻቪቻሎቫ ተከሳሽ ሩሲያ፤ ከሳሽ ቼፕሩኖቪና ሌሎች ተከሳሽ ሩሲያ፤ ከሳሽ ኖቫኮቭስካያ ተከሳሽ ሩሲያ፤ ከሳሽ ኦጎሮድኒኮቭና ሌሎች ተከሳሽ ሩሲያ እንዲሁም ከሳሽ ዣሪኖቫ ተከሳሽ ሩሲያ