ሰኔ 10, 2020
ሩሲያ
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ታሪካዊ ውሳኔ ካስተላለፈ አሥር ዓመት ቢያልፍም ሩሲያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መጣሷን ቀጥላለች
ከአሥር ዓመት በፊት፣ ሰኔ 10, 2010 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የሩሲያ ባለሥልጣናት የወንድሞቻችንን የአምልኮ ነፃነት በመጫን ለዓመታት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሲያደርሱባቸው እንደቆዩ የሚገልጽ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሩሲያ ዳጎስ ያለ ካሳ እንድትከፍልና በሞስኮ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት ዳግመኛ እንድትመዘግብ የሚያዝዝ ነበር፤ ባለሥልጣናቱ በ2004 የይሖዋ ምሥክሮችን ምዝገባ ሰርዘው ነበር።
የሞስኮ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ሊቀ መንበር የነበረው ወንድም ኢቫድ ቻይኮቭስኪ ይህ ውሳኔ እንደተላለፈ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቶ ነበር፦ “ይህ ብይን ምክንያታዊነት ሃይማኖታዊ አድልዎን እንደሚያሸንፍ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይህ ውሳኔ ባለሥልጣናቱ ሕጋዊ መብታችንን በአፋጣኝ እንዲመልሱልንና መንግሥት በመላዋ አገሪቱ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያደርሰውን ስደት እንዲያቆም እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ።”
ሆኖም ተስፋው እውን አልሆነም። የሩሲያ ባለሥልጣናት የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ ካለማክበራቸውም በላይ በመላዋ አገሪቱ በሚኖሩ ወንድሞቻችን ላይ የሚያደርሱትን ስደት አፋፍመው ቀጠሉ። የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰላማዊ በሆነው አምልኳችን ላይ እገዳ የሚጥል ውሳኔ በ2017 ባስተላለፈበት ወቅት ደግሞ ስደቱ በእጅጉ ተባባሰ፤ ይህ ኢፍትሐዊ ብይን ከተላለፈ በኋላ በርካታ ወንድሞቻችን ለክስና ለእስር ተዳርገዋል።
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ውሳኔውን ካስተላለፈ አሥር ዓመት ቢያልፈውም በሩሲያ ላይ ያስተላለፈው ከባድ ውሳኔ ዛሬም ድረስ ይሠራል። ፍርድ ቤቱ በ2010 ያስተላለፈው ውሳኔ ሩሲያ አሁንም ድረስ ሰላማዊ በሆኑት የእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ የምትሰነዝራቸው ክሶች ውድቅ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው።
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ ማጠቃለያ ላይ የሞስኮ የፍትሕ ጉዳዮች መሥሪያ ቤትና የሞስኮ ፍርድ ቤቶች የይሖዋ ምሥክሮች ዳግመኛ እንዳይመዘገቡ ለመከልከል የሚያስችል “ሕጋዊ መሠረት” እንደሌላቸው ደምድሟል። በተጨማሪም የሞስኮ ባለሥልጣናት “እንደ ባለሙያ ከእነሱ የሚጠበቀውን ፍትሐዊነትና ገለልተኝነት” እንዳላሳዩ በመግለጽ ተችቷቸዋል። ከዚህም ሌላ የሞስኮ ባለሥልጣናት ሩሲያም አባል የሆነችበትን የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት እንደጣሱ ተገልጿል።
እንደ 2010 ሁሉ በ2020ም ሩሲያ በወንድሞቻችን ላይ የምታደርሰውን ስደት ያስተዋሉ አካላት አሉ። ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው ድርጅት የአውሮፓና የማዕከላዊ እስያ ቅርንጫፍ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሬቸል ዴንበር እንዲህ ብለዋል፦ “በሩሲያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አምልኳቸውን ማከናወናቸው በነፃነታቸው ላይ አደጋ ይጥልባቸዋል።” በተጨማሪም ጥር 9, 2020 በሰጡት መግለጫ ላይ “እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ የሚያበቃ ምንም መሠረት የለም” ብለዋል።
በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብዙ በደል ቢደርስባቸውም ይሖዋ “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት” እንዲቋቋሙ ኃይል እንደሚሰጣቸው በመተማመን ለእነሱ መጸለያችንን እንቀጥላለን።—ቆላስይስ 1:11