ሰኔ 8, 2022
ሩሲያ
የአውሮፓ ፍርድ ቤት፣ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት በማድረሷ ሩሲያን የሚያወግዝ ታሪካዊ ውሳኔ አሳለፈ
ሰኔ 7, 2022 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት በማድረሷ ሩሲያን የሚያወግዝ ታሪካዊ ውሳኔ a አሳለፈ። ፍርድ ቤቱ ሩሲያ በ2017 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ መጣሏ ተገቢ እንዳልነበር ገልጿል። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ፣ የታተሙ ጽሑፎችንም ሆነ jw.orgን ማገዷ ሕገ ወጥ እንደሆነ ተናግሯል። ሩሲያ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የመሠረተቻቸውን ክሶች በሙሉ እንድታቋርጥ እንዲሁም እስር ላይ ያሉትን ሁሉ እንድትፈታ ታዛለች። በተጨማሪም ሩሲያ፣ የወረሰቻቸውን ንብረቶች ሁሉ እንድትመልስ ወይም ለንብረቶቹ ካሳ እንዲሆን 59,617,458 ዩሮ (63,684,978 የአሜሪካ ዶላር) እንድትከፍል ተጠይቃለች። ሩሲያ ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ የ3,447,250 ዩሮ (3,682,445 የአሜሪካ ዶላር) ካሳ እንድትከፍል ታዛለች።
ውሳኔው ከ2010 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት የቀረቡ 20 ክሶችን የሚመለከት ነው፤ እነዚህ ክሶች ግለሰቦችንና ሕጋዊ ማዕከላትን ጨምሮ ከ1,400 የሚበልጡ አቤቱታ አቅራቢዎችን ይመለከታሉ። ይሁንና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚነካው አቤቱታ አቅራቢዎቹን ብቻ አይደለም። ውሳኔው፣ ሩሲያ “በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተመሠረቱ የወንጀል ክሶችን በሙሉ ለማቋረጥና . . . ነፃነታቸውን የተነጠቁ የይሖዋ ምሥክሮችን በሙሉ ለማስለቀቅ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ መውሰድ” እንዳለባት ይገልጻል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ውሳኔው በሩሲያ ውስጥም ሆነ ከሩሲያ ውጭ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሙሉ ሕግ አክባሪ ዜጎች እንደሆኑና ፍርድ የሚተላለፍባቸውም ሆነ የሚታሰሩት ያለአግባብ እንደሆነ በሕግ የሚያረጋግጥ ብይን ነው።
ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ፣ ሩሲያ እንቅስቃሴያችን፣ እምነታችን፣ ጽሑፎቻችን እንዲሁም ድረ ገጻችን ጽንፈኛ እንደሆኑ መግለጿ መሠረተ ቢስ እንደሆነ በሚገባ ተብራርቷል። ለምሳሌ በውሳኔው ውስጥ የሚገኙትን የሚከተሉትን ሐሳቦች ልብ በል፦
እንቅስቃሴዎች፦ የሩሲያ ፍርድ ቤቶች “አቤቱታ አቅራቢዎቹ ንግግራቸው፣ ድርጊታቸው ወይም እንቅስቃሴያቸው በዓመፅ፣ በጥላቻ ወይም በመድልዎ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚያሳይ አንድም ማስረጃ” እንዳላቀረቡ ፍርድ ቤቱ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (§271)
የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንደያዙ ያላቸው እምነት፦ “የራስ ሃይማኖት የተሻለ እንደሆነ በሰላማዊ መንገድ ለማሳመን መሞከር እንዲሁም ሌሎች ‘የሐሰት ሃይማኖቶችን’ ትተው ወደ ‘እውነተኛው ሃይማኖት’ እንዲመጡ ማበረታታት የሃይማኖትና የመናገር ነፃነትን መጠቀም የሚቻልበት ሕጋዊ መንገድ ነው።” (§156)
ደም መውሰድ፦ “በስምምነቱም ሆነ በሩሲያ ሕግ መሠረት አንድ የማኅበረሰቡ አባል ሕክምናን በተመለከተ የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብት አለው፤ በመሆኑም ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆኗ ይህን መብቷን እንደተጠቀመችበት ያሳያል።” (§165)
ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፦ “በሃይማኖታዊ አመለካከት ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን የትኛውንም የሩሲያ ሕግ አይጥስም።” (§169)
ጽሑፎቻችን፦ “የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችና የጽሑፎቻቸው ይዘት ሰላማዊ ይመስላል፤ ይህም እንከተላለን ከሚሉት ከዓመፅ ነፃ የመሆን መርሕ ጋር ይስማማል።” (§157)
JW.ORG፦ ፍርድ ቤቱ jw.org ላይ ያሉት ነገሮች ጽንፈኝነት የሚንጸባረቅባቸው እንዳልሆኑ ገልጿል። ባለሥልጣናቱ ድረ ገጹ ላይ የወጡት አንዳንድ መረጃዎች ተገቢ እንዳልሆኑ ከተሰማቸው ሙሉውን ድረ ገጽ ከማገድ ይልቅ ድርጅቱ እነዚያን መረጃዎች እንዲያጠፋ መጠየቅ ነበረባቸው። (§231 እና §232)
ውሳኔው የሩሲያ ባለሥልጣናት መድልዎ እንደፈጸሙና “በሐቀኝነት እንዳልፈረዱ” በመግለጽ በጥብቅ አውግዟቸዋል። (§187) ለምሳሌ ፍርድ ቤቱ የደረሰባቸውን የሚከተሉትን ድምዳሜዎች ተመልከት፦
“በሩሲያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በሙሉ እንዲዘጉ የተደረገው ሕጋዊ በሆነ ምክንያት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሩሲያ ባለሥልጣናት ይህን ውሳኔ ያደረጉት የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ስለሚቃወሙና የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን እንዲተዉ እንዲሁም ሌሎች ሃይማኖቱን እንዳይቀላቀሉ ስለሚፈልጉ እንደሆነ ማስረጃው ይጠቁማል።” (§254)
የሩሲያ ባለሥልጣናት ከባድ “የአሠራር ችግር” እንዲኖር ፈቅደዋል፤ ለምሳሌ የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽሑፎቹን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ከመመርመር ይልቅ ፖሊሶችና አቃቤ ሕጉ የመረጡትን መድልዎ የሚንጸባረቅበት የምሁራን ሪፖርት መሠረት በማድረግ ውሳኔ አስተላልፏል። (§203)
ስለ ጽንፈኝነት የሚገልጸው ሕግ የተጻፈው ሰፊና አሻሚ በሆነ መንገድ መሆኑ ባለሥልጣናቱ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ አግባብ ያልሆነ ድርጊት እንዲፈጽሙባቸው መንገድ ከፍቷል። (§272)
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሩሲያ ውስጥ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ አናውቅም። ሆኖም ተስፋችንን የምንጥለው በሰብዓዊ ባለሥልጣናት ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ረዳታችንና ጋሻችን” የሆነውን “ይሖዋን በተስፋ እንጠባበቃለን።”—መዝሙር 33:20
a የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያወጣውን የሰባት ገጽ ጠቅለል ያለ ሐሳብ አውርድ። ሙሉውን የ196 ገጽ ውሳኔ አውርድ።