ጥቅምት 14, 2019
ሩሲያ
የወንድም ቫለሪ ሞስካሌንኮ የመደምደሚያ ንግግር
ዓርብ፣ ነሐሴ 30, 2019 ወንድም ቫለሪ ሞስካሌንኮ ለፍርድ ቤቱ የመደምደሚያ ንግግሩን አቅርቧል። በሩሲያኛ የቀረበው ንግግር ተተርጉሞ ከዚህ በታች በከፊል ቀርቧል፦
ክቡር ፍርድ ቤት እና እዚህ የታደማችሁ በሙሉ፣ በአሁኑ ወቅት 52 ዓመቴ ነው። ከታሰርኩ አንድ ዓመት አልፎኛል።
በዚህ ችሎት የመደምደሚያ ንግግሬ ላይ ስለ ራሴ፣ ስለ ወንጀል ክሱ እንዲሁም ስለ ሕይወት ያለኝን አመለካከት በተመለከተ ጥቂት ሐሳቦችን መናገር እፈልጋለሁ። በአምላክ ማመኔን የማልተወው እንዲሁም በአምላክ ማመን ወንጀል ያልሆነው ለምን እንደሆነ ክቡር ፍርድ ቤቱ ይረዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት ከጊዜ በኋላ ነው። ወላጆቼ ጥሩ ሰዎች ነበሩ እንዲሁም ጥሩ አስተዳደግ ነበረኝ፤ ያም ሆኖ ከልጅነቴ ጀምሮ በየቦታው የማየው ኢፍትሐዊነት ሰላም ይነሳኝ ነበር። ክፉዎችና አታላዮች ሲሳካላቸው፣ ታማኝና ደግ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ሲሠቃዩ ሳይ ‘ይህ መሆኑ ልክ አይደለም’ ብዬ አስብ ነበር።
በ24 ዓመቴ መጽሐፍ ቅዱስን ለበርካታ ወራት ካጠናሁና ከመረመርኩ በኋላ ለጥያቄዎቼ መልስ አገኘሁ።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ማንኛውንም ውሳኔ ሳደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዝርዝር የሰፈሩትን የአምላክ ሕጎችና መመሪያዎች ብሎም የእሱን አስተሳሰብ ከግምት ለማስገባት እንዲሁም ጥንት የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች የተዉትን ምሳሌ ለመከተል እሞክራለሁ።
ከእናቴ ጋር አብረን ነው የምንኖረው። እናቴ በዕድሜ የገፋች ስለሆነች የእኔ እንክብካቤ ያስፈልጋታል። ነሐሴ 1, 2018 እናቴ ቤት ውስጥ ብቻዋን ነበረች፤ በዚያ ቀን የፌደራል ደህንነት አገልግሎት (FSB) መርማሪው፣ ልዩ ኃይሎች የበራችንን ማጠፊያ በመጋዝ ቆርጠው ወደ ቤት እንዲገቡ ትእዛዝ ሰጠ። መርማሪው ቤታችን እንዲፈተሽ ያደረገው በዚህ መልኩ ነበር።
በወቅቱ እናቴ በጣም ፈርታ ነበር። ጭምብል ያጠለቁት ልዩ ኃይሎች በሩን ሰብረው ወደ ቤታችን ሲገቡ እናቴ የልብ ድካም ስለያዛት አንቡላንስ ተጠራ። ቤቴ ውስጥ ፖሊሶች እንደገቡ ከሰማሁ ከ30 ደቂቃ በኋላ ቤት ደረስኩ። እናቴ ያለችበትን ሁኔታ ስመለከት የእኔም የደም ግፊት በኃይል ጨመረ። በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም አልተቆጣሁም፤ ከዚህ ይልቅ ለመረጋጋት ሞከርኩ። ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቀውን ደግነት ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ደግነት እንዳሳይ ያስተማረኝን አምላኬን ይሖዋን ማሳዘን አልፈልግም።
ይቅርታ ይደረግልኝና ክቡር ፍርድ ቤት፣ ስለ ራሴ ብዙ ማውራት የምወድ ሰው አይደለሁም። አሁን ግን መናገሬ የግድ ነው።
የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ 25 ዓመት አልፎኛል። ይህም የዕድሜዬን ግማሽ እንደማለት ነው። ይህን ሁሉ ዓመት እንደ ጽንፈኛ ተቆጥሬ አላውቅም። ከዚህ ይልቅ የምታወቀው ጥሩ ጎረቤትና ታታሪ ሠራተኛ በመሆን እንዲሁም እናቴን በመንከባከብ ነው።
ሚያዝያ 20, 2017 በድንገት ጽንፈኛ የሚል ስም ተሰጠኝ። ምን አድርጌ ነው? ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ? ባሕርዬ ተበላሽቶ ነው? አይደለም። ዓመፀኛ ሆኜ ወይም ሰዎችን አሠቃይቼ ነው? አይደለም። በሩሲያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 28 ላይ የሰፈረውን መብት አጥቼ ነው? ይህም አይደለም። ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባደረገው ውሳኔ ላይ ስሜ አልተጠቀሰም። አንቀጽ 28ን ጨምሮ የሩሲያ ሕገ መንግሥት የሰጠኝን መብት ማንም ተቃውሞ አያውቅም። ታዲያ ተከስሼ ፊታችሁ የቀረብኩት ለምንድን ነው?
ከመርማሪው ጋር ስነጋገር በግልጽ መረዳት እንደቻልኩት፣ የታሰርኩት ሉዓላዊ አምላክ በሆነው በይሖዋ በማመኔና በንግግሬም ሆነ በጸሎቴ ላይ ስሙን በመጠቀሜ ነው። ሆኖም ይህ ወንጀል አይደለም። ይህን ስም የመረጠውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር ያደረገው አምላክ ራሱ ነው።
አሁንም ደጋግሜ የምናገረው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከሰፈረው የአምላክ ፈቃድ ጋር የማይስማማ ነገር ማድረግ ፈጽሞ የማላስበው ነገር እንደሆነ ነው። ምንም ያህል ጫና ቢደረግብኝ ወይም ቅጣት ቢደርስብኝ አሊያም ሞት ቢፈረድብኝም እንኳ የጽንፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋ አምላክን እንደማልተው በግልጽ እናገራለሁ።
ክቡር ፍርድ ቤት፣ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚታወቁት አፍቃሪና ሰላም ወዳዶች በመሆናቸው ነው። የአምልኮ መብታቸው በበርካታ አገሮች ውስጥ ተከብሮላቸዋል። በመሆኑም የእኔም ሆነ የሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች መብት በሩሲያ ውስጥም እንዲከበር ያለኝን ፍላጎት እገልጻለሁ።
ወንጀለኛ አይደለሁም፤ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲለቀኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ!
አመሰግናለሁ!