በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሲምዮን ባይባክ

ኅዳር 25, 2020
ሩሲያ

የወንጀል ክስ የቀረበበት ወጣቱ ወንድም ሲምዮን ባይባክ በእምነቱ ምክንያት ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው

የወንጀል ክስ የቀረበበት ወጣቱ ወንድም ሲምዮን ባይባክ በእምነቱ ምክንያት ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

በሮስቶቭ ኦን ዶን የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት የወንድም ሲምዮን ባይባክን ጉዳይ ተመልክቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ለታኅሣሥ 18, 2020 a ቀጠሮ ይዟል። አቃቤ ሕጉ፣ ወንድም ሲምዮን ባይባክ የአራት ዓመት የገደብ እስር እንዲፈረድበት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

አጭር መግለጫ

ሲምዮን ባይባክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1997 (ሮስቶቭ ኦን ዶን)

  • ግለ ታሪክ፦ ታላቅ ወንድምና እህት አለው። ቻይንኛ ተምሮ፣ ቻይንኛ በማስተማር ይተዳደራል። ግጥም ማንበብና መጻፍ ይወዳል

  • ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ወላጆቹ ስለ ይሖዋ አስተምረውታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ስለተማረ እያደገ ሲሄድ ሕይወቱን በዚያ መሠረት ለመምራት ወስኗል። በሃይማኖታዊ አቋሙ የተነሳ ሕሊናው ስላልፈቀደለት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም ከ2015 እስከ 2017 በአካባቢው በሚገኝ የልጆች ሆስፒታል ውስጥ የጽዳት ሠራተኛ በመሆን አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ሰጥቷል።

የክሱ ሂደት

ጽንፈኝነትን ለመዋጋት በተቋቋመው ማዕከል ውስጥ የሚሠሩ ፖሊሶች፣ ግንቦት 22, 2019 ሮስቶቭ ኦን ዶን ውስጥ የ13 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶችን በረበሩ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ማለትም ሰኔ 6, 2019 ወንድም ሲምዮን የወንጀል ፋይል ተከፈተበት። በዚህም የተነሳ በቁጥጥር ሥር ውሎ ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ ለአንድ ቀን ታሰረ፤ በኋላም የቁም እስረኛ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ አዘዘ። መጀመሪያ ላይ የተፈረደበት ስምንት ሳምንት የቁም እስረኛ ሆኖ እንዲቆይ ነበር፤ ሆኖም ይህ ጊዜ ሰባቴ ተራዝሟል።

መጀመሪያ ላይ ፖሊስ “ወንጀል” ብሎ ያቀረበው ክስ፣ በሃይማኖታዊ ስብሰባዎች ላይ መካፈሉንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማረውን ነገር ለሌሎች መናገሩን ነው። ኅዳር 2019 ደግሞ “በጽንፈኝነት” ለተፈረጀ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል የሚል ክስ ቀረበበት።

በሩሲያ ባሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የሚደርሰው ስደት አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ሆኖም “የሰላም አምላክ” የሆነው ይሖዋ ‘ፈቃዱን ለማድረግ’ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚያሟላላቸው እንተማመናለን።—ዕብራውያን 13:20, 21

a ቀኑ ሊለወጥ ይችላል