በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከላይ፦ ወንድም አሌክሲ ቡደንቹክ፣ ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን፣ ወንድም ጀናዲ ጀርመን እና ወንድም ሮማን ግሪዳሶቭ ከታች፦ ወንድም ቫዲም ኩትሰንኮ፣ ወንድም ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ እና ወንድም አሌክሲ ሚረትስኪ

ኅዳር 6, 2020
ሩሲያ

የዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ባለሥልጣናት ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የምታደርሰውን ስደት ተቃወሙ

የዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ባለሥልጣናት ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የምታደርሰውን ስደት ተቃወሙ

“ዓይን ያወጣ የፍትሕ ጥሰት።”—ጌይል ማንቺን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን ሊቀ መንበር

የአውሮፓና የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት በሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እየደረሰ ያለውን ስደት ማውገዛቸውን ቀጥለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን

“የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን፣ ሩሲያ በዴኒስ ክሪስተንሰን ላይ በምታደርሰው በደል በጣም አዝኗል” በማለት ሊቀ መንበር ጌይል ማንቺን ጥቅምት 27, 2020 በወጣ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ሊቀ መንበሯ አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ባለሥልጣናቱ ይህን ምስኪን ሰው መበቀል እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው፤ ይህ ሰው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከማከናወን ውጭ ያጠፋው ነገር የለም። መንግሥት ለዚህ ሰው ምሕረት ከማድረግ ይልቅ እንደ አደገኛ ወንጀለኛ ቆጥሮ በደል እያደረሰበት ነው። ይህ ዓይን ያወጣ የፍትሕ ጥሰት ነው።”

ሊቀ መንበር ጌይል ማንቺን፣ በኮሚሽኑ ሥር ባለው በሕሊናቸው ምክንያት የታሰሩ ሃይማኖታዊ እስረኞች ፕሮጀክት አማካኝነት ለወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን እየታገሉ ነው። ኮሚሽኑ በዴኒስ ክሪስተንሰን ላይ የተበየነውን የስድስት ዓመት እስራት በተደጋጋሚ በጥብቅ ሲያወግዝ ቆይቷል።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ የሩሲያ መንግሥት፣ ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን በአመክሮ እንዳይፈታ ማድረጉንም አውግዟል። የኮሚሽኑ ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “[ዴኒስ ክሪስተንሰን] በአመክሮ እንዲፈታ ሰኔ 23 [2020] ተፈርዶለት የነበረ ቢሆንም አቃቤ ሕጉ ወዲያውኑ ውሳኔውን ተቃወመ። በመሆኑም ዴኒስ ክሪስተንሰን መፈታቱ ቀረና የእስር ቤቱን ደንብ ተላልፏል በሚል ክስ በቂ አየር በማያገኝ የእስረኞች መቅጫ ክፍል ውስጥ እንዲታሰር ተደረገ።”

ኮሚሽኑ ሪፖርቱን የደመደመው የ2020 ዓመታዊ ሪፖርቱን በመጥቀስ ነው። ሪፖርቱ የሩሲያ መንግሥት የሚያካሂደውን “የተቀነባበረ፣ ቀጣይና ዓይን ያወጣ የሃይማኖታዊ ነፃነት ጥሰት” አውግዟል፤ በተጨማሪም ኮሚሽኑ፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሩሲያን “በጣም አሳሳቢ አገር” በማለት ቅጣት እንዲበይንባት ሐሳብ አቅርቧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ

በተመሳሳይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የተሾሙ ስምንት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ በሩሲያ ፌዴሬሽን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ ተጠሪ በአንድነት በላኩት ደብዳቤ ላይ “በሩሲያ ፌዴሬሽን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች እየደረሰባቸው ባለው ስደት፣ በሴንት ፒተርስበርግ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር ማዕከል እንዲፈርስ በመደረጉ እንዲሁም በ395ቱም ቅርንጫፎች በሚከናወነው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ላይ እገዳ በመጣሉ” የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። ሩሲያ ስደቱን እንድታቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ ያቀረበላትን ጥሪ ችላ በማለቷም ባለሥልጣናቱ ተችተዋታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት እንደተናገሩት በግልጽ ያልተቀመጠው የሩሲያ የጽንፈኝነት ሕግ “የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ማንኛውንም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ለመከልከል፣ በመካከላቸው ፍርሃት ለመዝራት፣ ፖሊሶች ቤታቸውን በመፈተሽና እነሱን በማንገላታት መብታቸውን እንዲጥሱ ለማድረግ፣ አንዳንድ አባሎቻቸውን ይዘው ለምርመራ ለማቅረብ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በእነሱ ላይ ለመፍረድና ለማሰር” ተሠርቶበታል።

ባለሥልጣናቱ “በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት a አንቀጽ 18 (1) መሠረት የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን የማካሄድ መብት” እንዳላቸው አበክረው ገልጸዋል። በመሆኑም ባለሥልጣናቱ በሩሲያ “በ2002 የወጣው ጽንፈኝነትን የሚዋጋ የፌዴራል ሕግ የግለሰቦችን የማሰብ፣ የሕሊና፣ የሃይማኖት ወይም የእምነት ነፃነት እንዳይጥስ” የሩሲያ ፌዴሬሽን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ደብዳቤው በወንድሞቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የጭካኔ ድርጊት አጋልጧል። ለምሳሌ በሳራቶቭ ከተማ በሚኖሩት አምስት ወንድሞች ላይ የካቲት 6, 2020 የደረሰውን ድብደባ ጠቅሷል። ደብዳቤው “በፖሊስ የተያዙት የይሖዋ ምሥክሮች በሃይማኖታቸው ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ በጣም ከባድ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚታሰሩ፣ ግፍ እንደሚፈጸምባቸው እንዲሁም ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትሉ ሌሎች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙባቸው” ገልጿል።

ባለሥልጣናቱ የላኩት ደብዳቤ፣ የሩሲያ መንግሥት የሚያደርሰውን ስደት የሚያሳይ ሌላ አሳዛኝ ምሳሌም ጠቅሷል፤ የካቲት 10, 2020 ፖሊሶች በወንድም ቫዲም ኩትሰንኮ ላይ ከፍተኛ ሥቃይ አድርሰውበታል። የሩሲያ ባለሥልጣናት ይህን እንዳላደረጉ ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ግን ይህ አላሳመናቸውም፤ እንዲያውም “በሩሲያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በመላ አገሪቱ እየደረሰባቸው ያለው የማያባራ አፈና” በጣም እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

የአውሮፓ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ምክር ቤት

ሩሲያ በ2017 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ ከጣለችና ስደት ማድረስ ከጀመረች ወዲህ የአውሮፓ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ምክር ቤት b አገሪቱ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፋቸውን ሁለት ውሳኔዎች እያከበረች መሆኑን በጥብቅ መከታተል ጀመረ። c በመሆኑም ኮሚቴው ጥቅምት 1, 2020 አንድ ውሳኔ አሳለፈ፤ በዚህ ውሳኔ ላይ “በ2017 የተጣለው እገዳ እና ከተለያዩ ምንጮች የሚሰማው አስደንጋጭ ሪፖርት” እንዳሳሰበው ገልጿል፤ እነዚህ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት “በእገዳው የተነሳ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸውን በማከናወናቸው ምክንያት ብቻ አሁንም እየተያዙ፣ ፍርድ ቤት እየቀረቡና እየታሰሩ ነው።”

ኮሚቴው እንዲህ ያሉ የመብት ጥሰቶችን ማስቀረት እንዲቻል ሩሲያ “የይሖዋ ምሥክሮች እገዳ እንዲጣልባቸውና እንዲከሰሱ መንገድ የከፈተውን አሁን ያለውን የፀረ ጽንፈኝነት ሕግ” እንድታሻሽል ሐሳብ አቅርቧል። በተጨማሪም ሩሲያ “የጣለችውን እገዳ ለማንሳትና ሰላማዊ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን በማከናወናቸው ምክንያት በተወነጀሉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተመሠረተውን ክስ ለመሰረዝ” ጥረት ልታደርግ እንደሚገባ ኮሚቴው ገልጿል። ኮሚቴው ሩሲያ ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል እርምጃ መውሰዷን በ2021 በድጋሚ ይገመግማል።

ከ2017 ወዲህ በሩሲያ እና በክራይሚያ የሚገኙ ከ400 የሚበልጡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጽንፈኝነት ወንጀል ተከሰዋል። ከ70 በሚበልጡ የሩሲያ ከተሞች ውስጥ ከ210 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ታስረዋል።

እኛም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በትዕግሥት መጽናታቸውን እንዲቀጥሉ እንዲረዳቸው በመለመን “የአምላካችንን የይሖዋን ስም እንጠራለን።”—መዝሙር 20:2, 7