በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አሌክሳንደር ኢቨሺን

የካቲት 12, 2021
ሩሲያ

የ63 ዓመቱ ወንድም አሌክሳንደር ኢቨሺን በኢንተርኔት አማካኝነት ስብሰባ በማደራጀቱና መዝሙር በመዘመሩ ምክንያት የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ተፈረደበት

የ63 ዓመቱ ወንድም አሌክሳንደር ኢቨሺን በኢንተርኔት አማካኝነት ስብሰባ በማደራጀቱና መዝሙር በመዘመሩ ምክንያት የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ተፈረደበት

የፍርድ ውሳኔ

የካቲት 10, 2021 በክራስኖዳር ክልል የሚገኘው የአብንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም አሌክሳንደር ኢቨሺን ላይ የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ፈርዶበታል። ይህ ፍርድ ድርጅቱ 2017 ከታገደ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከተጣለው ቅጣት ሁሉ ከባዱ ነው።

አጭር መግለጫ

አሌክሳንደር ኢቨሺን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1957 (ካታቭ-ኢቫኖቭስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ጡረታ ከመውጣቱ በፊት የቅርጽ ማውጫ ማሽን ባለሙያ፣ ዛፍ ቆራጭ እና የኢንዱስትሪ ደህንነት መሐንዲስ ሆኖ ሠርቷል። በ1974 ከገሊና ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለት ሴት ልጆችና ስምንት የልጅ ልጆች አሏቸው

    በከባድ ሕመም ከተያዘ በኋላ ስለ ሕይወት ዓላማ ማሰብ ጀመረ። ከአራቱ ወንጌሎች ሦስቱን በአንድ ሌሊት አንብቦ ከጨረሰ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ1995 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

በአቢንስክ በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ሕግን መሠረት ያደረገ ጥቃት መሰንዘር የተጀመረው ከ2015 መጀመሪያ አንስቶ ነው። በአካባቢው የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት “ጽንፈኛ” ተብሎ ታገደ። ከአምስት ዓመት ገደማ በኋላ ማለትም ሚያዝያ 23, 2020 በወንድም አሌክሳንደር ኢቨሺን ላይ የወንጀል ክስ ተመሠረተ። ወንድም አሌክሳንደር ኢቨሺን ከተከሰሰባቸው “ወንጀሎች” መካከል በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ሃይማኖታዊ ስብሰባ ማደራጀትና የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመር ይገኙበታል።

ፖሊሶች የአሌክሳንደርንና የገሊናን ቤት በበረበሩበት ወቅት ሁለቱም በድንጋጤ የደም ግፊታቸው በጣም ከፍ ብሎ ነበር። ፍተሻው ከተካሄደ ከተወሰኑ ወራት በኋላ የአሌክሳንደር መኪና ተወረሰ። አሌክሳንደር እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ቀጥሏል። ለፍርድ ቤቱ የመደምደሚያ ሐሳቡን በተናገረበት ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ተከስሼ በፍርድ ቤት መቆሜ ምንም አያስገርመኝም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ይህ እንደሚሆን ትንቢት ተናግሯል። በማቴዎስ 10:18 ላይ ‘ደግሞም በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ መመሥከር ትችላላችሁ’ ብሏል። . . . ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ለፍርሃት አይዳርገኝም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ሰዎች ሁሉ ስለሚጠብቃቸው ተስፋ ለተከበረው ፍርድ ቤት መናገር በመቻሌ በጣም ደስታ ይሰማኛል።”

አሌክሳንደርና ገሊና በሩሲያም ሆነ በመላው ዓለም ለሚሰጠው ታላቅ ምሥክርነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። ይሖዋ በእሱ በመታመናቸው አትረፍርፎ እንደሚባርካቸው እርግጠኞች ነን።—ኤርምያስ 17:7