ጥር 26, 2021
ሩሲያ
የ77 ዓመት አዛውንት የሆኑት ወንድም ቭላድሚር ፊሊፖቭ የስድስት ዓመት ተኩል እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
በፕሪሞርይስ ክልል የሚገኘው የናደዠዲንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት የወንድም ቭላድሚር ፊሊፖቭን ጉዳይ ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ጥር 27, 2021 a ቀጠሮ ይዟል። ወንድም ቭላድሚር ፊሊፖቭ የስድስት ዓመት ተኩል እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል።
አጭር መግለጫ
ቭላድሚር ፊሊፖቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1943 (ኦክትያቢርስኪ፣ ኖቮሰቢርስክ ክልል)
ግለ ታሪክ፦ ወንድም ቭላድሚር ፊሊፖቭ ከመወለዳቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት አባታቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሞቱ። በ1964 ከቶምስክ የጦር ትምህርት ቤት የሌተና ማዕረግ ይዘው ተመረቁ። በ1967 ከልዩቦቭ ጋር ትዳር መሠረቱ። ጡረታ ከመውጣቸው በፊት በጦር ሠራዊት ውስጥ 27 ዓመት አገልግለዋል
በ1994 ባለቤታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንድም ፊሊፖቭም ማጥናት ጀመሩ። ሁለቱም በቀጣዩ ዓመት ተጠመቁ
የክሱ ሂደት
ነሐሴ 2017 ባለሥልጣናቱ ወንድም ፊሊፖቭ እና በራዝዶልኖዬ ያሉ ሌሎች ወንድሞች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በድብቅ መቅረጽ ጀመሩ። ለተወሰኑ ወራት ያህል ባለሥልጣናቱ ወንድም ፊሊፖቭ በስብሰባዎች ላይ ንግግር ሲያቀርቡ እንዲሁም ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲወያዩ ይቀርጿቸው ነበር።
ሐምሌ 19, 2018 መሣሪያ የታጠቁና ጭምብል ያጠለቁ የፌዴራል ደህንነት አባላት የእነወንድም ፊሊፖቭን ቤት ሰብረው ገቡ። የደህንነት አባላቱ ወንድም ፊሊፖቭን ፊታቸው ላይ በቡጢ ከመቷቸው በኋላ መሬት ላይ አስተኝተው እጃቸውን የኋሊት አሠሯቸው፤ ከዚያም ቤታቸውን በረበሩት፤ በወቅቱ ወንድም ፊሊፖቭ 75 ዓመታቸው ነበር። ከዚያ በኋላ የእነወንድም ፊሊፖቭ ቤት ነሐሴ 2019 እና ጥር 2020 በድጋሚ ተበርብሯል። ለሁለተኛ ጊዜ ቤታቸው ከተበረበረ በኋላ ወንድም ፊሊፖቭ የወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው።
ይሖዋ፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ደስታቸውንና እምነታቸውን ጠብቀው ለመቀጠል የሚያስፈልጋቸውን ኃይልና ብርታት እንዲሰጣቸው እንመኛለን!—ኢሳይያስ 40:29, 31
a ቀኑ ሊቀየር ይችላል።