በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ቫሲሊ ርዬዝኒችዬንኮ

መጋቢት 26, 2021
ሩሲያ

የ78 ዓመቱ ወንድም ቫሲሊ ርዬዝኒችዬንኮ በሰላማዊ መንገድ አምልኳቸውን በማካሄዳቸው “በጽንፈኝነት” ተከሰሱ

የ78 ዓመቱ ወንድም ቫሲሊ ርዬዝኒችዬንኮ በሰላማዊ መንገድ አምልኳቸውን በማካሄዳቸው “በጽንፈኝነት” ተከሰሱ

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም ቫሲሊ ርዬዝኒችዬንኮ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

ሐምሌ 30, 2021 የአሙር ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ቫሲሊ ርዬዝኒችዬንኮ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል። በመሆኑም መጀመሪያ ላይ የተፈረደባቸው የሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት በዚያው ጸንቷል። እርግጥ ወንድም ቫሲሊ አሁን ወህኒ አይወርዱም።

ሰኔ 2, 2021 በአሙር ክልል የሚገኘው የዝዬያ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ቫሲሊ ርዬዝኒችዬንኮ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ውሳኔ አሳልፏል። ወንድም ቫሲሊ የሁለት ዓመት የገደብ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

አጭር መግለጫ

ቫሲሊ ርዬዝኒችዬንኮ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1942 (ሙሮቭካ፣ ፕሪሞርይስ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ከአምስት ልጆች የመጨረሻው ናቸው። ትራክተር እና መርከብ መንዳት ተምረዋል፤ እንዲሁም በሜካኒክነት ሠልጥነዋል። በጦር ሠራዊት ውስጥ አገልግለዋል። የውትድርና አገልግሎታቸውን ሲያጠናቅቁ መርከብ ላይ የሠሩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ የካፒቴንነት ማዕረግ አግኝተዋል። “ቬተራን ኦቭ ሌበር ኦቭ ዘ ሶቪየት ዩኒየን” የሚል የክብር ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል

    በ1969 ከቫለንቲና ጋር ትዳር መሠረቱ። ሦስት ወንዶች ልጆች አሳድገዋል። በ1990ዎቹ ዓመታት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከቫለንቲና ሰሙ። ቫሲሊ አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ ከተማሩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት አጠኑ። በ1996 ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር ሆኑ። በ2016 ባለቤታቸውን በሞት አጥተዋል

የክሱ ሂደት

መጋቢት 21, 2019 በዝዬያ ከተማ የሚገኙ ፖሊሶች የወንድም ቫሲሊ ርዬዝኒችዬንኮን ቤት ፈተሹ። ከዚያም የወንድማችንን ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ ሞባይል ስልክ እንዲሁም የግል መረጃዎች ወሰዱ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ወንድም ርዬዝኒችዬንኮ፣ ሩሲያ ውስጥ “በጽንፈኝነት” በተፈረጁ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ከመሆኑም ሌላ የባንክ ሒሳባቸውን መጠቀም እንዳይችሉ ተከልክለዋል። አካባቢያቸውን ለቅቀው መሄድም አልተፈቀደላቸውም።

ወንድም ርዬዝኒችዬንኮ በይሖዋ እርዳታ መታመናቸውን ቀጥለዋል። ጥሩ መንፈሳዊ ልማዳቸውን ይዘው መቀጠላቸው እንዲረጋጉ ረድቷቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስን እና የዕለቱን ጥቅስ በየቀኑ ያነባሉ። በተጨማሪም የወንድም ርዬዝኒችዬንኮ የእምነት አጋሮች በፍቅር ይንከባከቧቸዋል፤ ለዚህም አመስጋኝ ናቸው።

እንዲህ ብለዋል፦ “ቤቴ በተፈተሸና የፖሊስ ምርመራ በተደረገብኝ ማግስት በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች መጥተው ጠየቁኝ። አንዳንዶቹ ወንድሞችም [ቤታቸው] ተፈትሾ ነበር። ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በአቅራቢያችን ባሉ ከተሞች የሚኖሩ የተወሰኑ ወንድሞች ሊጠይቁኝ መጡ። ይህን ያደረጉት ነፃነታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነው። ጉብኝታቸው በጣም አበረታቶኛል። አሁንም እንኳ ሳስበው እንባዬ ይመጣል።” አክለውም “እነዚህ ሁኔታዎች ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና አጠናክረውታል። ይበልጥ ወደ እሱ እንደቀረብኩ ይሰማኛል” ብለዋል።

ወንድም ርዬዝኒችዬንኮ በዕብራውያን 13:5 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ብርታትና መጽናኛ እንደሰጣቸው ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋ ‘ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ በማለት በገባው ቃል ምንጊዜም ለመታመን ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ።” ይሖዋ በእምነታቸው ምክንያት ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መደገፉን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።