በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 25, 2020
ሩሲያ

ዴኒስ ክሪስተንሰን ሩሲያ ውስጥ ከታሰረ ሦስት ዓመት ሆነው፤ አሁንም በደስታ እንደጸና ነው

ዴኒስ ክሪስተንሰን ሩሲያ ውስጥ ከታሰረ ሦስት ዓመት ሆነው፤ አሁንም በደስታ እንደጸና ነው

ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን ሩሲያ ውስጥ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ከታሰረ ዛሬ ሦስት ዓመት ሞልቶታል። ግንቦት 25, 2017 ከታሰረበት ጊዜ አንስቶ አንዳንድ ጓደኞቹ “የደረሰብህ መከራ በእምነትህ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮብሃል?” በማለት ይጠይቁታል። የእሱ መልስ ግን ሁሌም አንድ ዓይነት ነው፤ “እምነቴ ይበልጥ ተጠናክሯል” ይላቸዋል።

ወንድም ክሪስተንሰን እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ ምዕራፍ 1 ቁጥር 2 እና 3 ላይ የሚናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን በሕይወቴ አይቻለሁ፦ ‘ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፤ ይህን ስታደርጉ ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ።’”

በጣም የሚያስገርመው ወንድም ክሪስተንሰን የሚደርስበት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታና መከራ ቢባባስም እምነቱም ሆነ ደስታው በእጅጉ ጨምሯል።

ወንድም ክሪስተንሰን በፖሊሶች ከተያዘ በኋላ ወዲያውኑ በኦርዮል ከሚገኘው ቤቱ እምብዛም በማይርቅ እስር ቤት ውስጥ ያለፍርድ እንዲቆይ ተደረገ። ከጊዜ በኋላም ባለቤቱ አይሪና እሱን መጠየቅ ተፈቀደላት። ወንድም ክሪስተንሰን ፍርድ ሳይሰጠው ለሁለት ዓመት በእስር ቆይቷል። የካቲት 2019 ወንድም ክሪስተንሰን የስድስት ዓመት እስር ተበየነበት። ይግባኝ የጠየቀ ቢሆንም ከሦስት ወር በኋላ ይግባኙ ውድቅ ተደረገ። በኋላም ከኦርዮል 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ እስር ቤት በመዛወሩ ከአይሪና ጋር ይበልጥ ተራራቁ።

ወንድም ክሪስተንሰን በአመክሮ ለመፈታት ብቃቱን ካሟላ አንድ ዓመት ሆኖታል። ያም ቢሆን እስካሁን ካቀረባቸው አራት ማመልከቻዎች ሦስቱ ውድቅ ሆነዋል። ወንድም ክሪስተንሰን እነዚህ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም በታማኝነት እንደጸና ነው።

ወንድም ክሪስተንሰን እንዲህ ሲል በትሕትና ተናግሯል፦ “እኔና አይሪና ፍጹማን አይደለንም። ያም ቢሆን በመከራ ውስጥ መጽናትና ደስታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተምረናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላካችንና አባታችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ ችለናል።”

ሩሲያ ውስጥ ስደትን በደስታ እየተቋቋሙ ያሉትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ይሖዋ እንደሚረዳቸው በመተማመን በልበ ሙሉነት በጸሎት እናስባቸዋለን።—ማቴዎስ 5:11, 12