በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አሌክሲ ኦሬሽኮቭ፣ ወንድም አሌክሳንደር ራኮቭስኪ እና ወንድም አሌክሳንደር ቫቪሎቭ

ሐምሌ 2, 2021
ሩሲያ

ጸሎትና ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች ሦስት ወንድሞች ስደትን በጽናት እንዲቋቋሙ ረድተዋቸዋል

ጸሎትና ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች ሦስት ወንድሞች ስደትን በጽናት እንዲቋቋሙ ረድተዋቸዋል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኛቸውን ውድቅ አደረገ

ጥር 14, 2022 የኒዥኒ ኖቭጎሮድ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም አሌክሲ ኦሬሽኮቭ፣ ወንድም አሌክሳንደር ራኮቭስኪ እና ወንድም አሌክሳንደር ቫቪሎቭ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። እርግጥ በአሁኑ ወቅት ወህኒ አይወርዱም።

ጥቅምት 25, 2021 በኒዥኒ ኖቭጎሮድ ክልል የሚገኘው የፓቭሎቭስኪ ከተማ ፍርድ ቤት ወንድም አሌክሲ ኦሬሽኮቭ፣ ወንድም አሌክሳንደር ራኮቭስኪ እና ወንድም አሌክሳንደር ቫቪሎቭ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላለፈ። ሦስቱም የሦስት ዓመት የገደብ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

አጭር መግለጫ

አሌክሲ ኦሬሽኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1971 (ፓቭሎቮ፣ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በልጅነቱ የጠረጴዛ ቴኒስ መጫወት ይወድ ነበር። ከሙዚቃ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ሲሆን በዋነኝነት የተማረው የትንፋሽ መሣሪያዎችን ነው። አሁን ጡረታ ወጥቷል። በዕድሜ የገፉ እናቱን ለዓመታት ተንከባክቧል። በ2011 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

አሌክሳንደር ራኮቭስኪ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1980 (ፓቭሎቮ፣ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በወጣትነቱ ጊታር መጫወት የተማረ ሲሆን የሙዚቃ ቡድን አባል ሆኖ ይጫወት ነበር። የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ባለሙያ ሆኖ ሠርቷል። በ2005 ከታትያና ጋር ትዳር መሠረተ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የያዘውን ተስፋ ካወቁ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመሩ። በ2009 ተጠመቁ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አላቸው

አሌክሳንደር ቫቪሎቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1967 (ክሮፖትኪን፣ ክራስኖዳር ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በወጣትነቱ ሩጫ፣ ዋና፣ የበረዶ ላይ ሸርተቴ እና ሥዕል ይወድ ነበር። በጦር ሠራዊት ውስጥ አገልግሏል። ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ ለመሆን ሠልጥኖ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ዓመፅ በሚንጸባረቅበት ስፖርት ላለመካፈል ወሰነ፤ ከዚያም ፀጉር አስተካካይ ሆነ። እሱና ባለቤቱ ዬሌና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። በ1994 ተጋቡ፤ በ1995 ተጠመቁ። ከቤት ውጭ ጊዜ ማሳለፍ ይወዳሉ

የክሱ ሂደት

የፌዴራል ደህንነት አባላት ሐምሌ 16 እና 17, 2019 በኒዥኒ ኖቭጎሮድ ክልል የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በረበሩ። በመሆኑም ወንድም አሌክሲ ኦሬሽኮቭ እና ወንድም አሌክሳንደር ቫቪሎቭ የወንጀል ምርመራ የተካሄደባቸው ሲሆን በኋላም ማረፊያ ቤት ገቡ። አሌክሲ 211 ቀን በማረፊያ ቤት ከቆየ በኋላ 31 ቀን በቁም እስር አሳልፏል። አሌክሳንደር በማረፊያ ቤት 241 ቀን ቆይቷል።

አሌክሲ ማረፊያ ቤት በነበረበት ወቅት ከቀድሞው ይበልጥ አዘውትሮና አጥብቆ ይጸልይ ነበር። በየቀኑ ከእንቅልፉ ሲነሳ በዕለቱ ስለሚያጋጥሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተገቢው አመለካከት እንዲኖረውና ታማኝነቱን እንዲጠብቅ እንዲሁም ስለ መንፈሳዊ ነገሮች እንዲያስብ ይጸልይ ነበር። በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦ “ምሽት ላይ የማቀርበው ጸሎት ይበልጥ ረጅም እና ይበልጥ ጥልቀት ያለው ነበር፤ ሁሉንም ወንድሞች በስም ለመጥቀስ ጥረት አደርግ ነበር። ስለ ማረፊያ ቤቱ ሠራተኞች፣ አብረውኝ ስለታሰሩት ሰዎች፣ ስለ መርማሪው፣ ስለ ቤተሰቤ፣ ስለ ጉባኤው እና ስለ ድርጅቱ እጸልይ ነበር።”

አሌክሳንደር ቫቪሎቭ እንዲህ ብሏል፦ “ከይሖዋ ጋር ይበልጥ ተቀራርቤያለሁ። በእጄ ይዞ እንደሚመራኝ ብቻ ሳይሆን አንድ እረኛ አንዲትን የበግ ግልገል እቅፍ እንደሚያደርጋት ሁሉ ይሖዋም በክንዶቹ እንዳቀፈኝ ይሰማኛል። የይሖዋ እንክብካቤ በየዕለቱ ይበልጥ ግልጽ ሆኖልኛል።”

መስከረም 21, 2020 አሌክሳንደር ራኮቭስኪም ክስ የተመሠረተበት ሲሆን ጉዳዩ ከወንድም አሌክሲ ኦሬሽኮቭ እና ከወንድም አሌክሳንደር ቫቪሎቭ ክስ ጋር መታየት ጀመረ። ሦስቱም ወንድሞች በይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ስብሰባ በመካፈላቸውና በሌሎች ጉዳዮች ተከሰዋል። የጉዞ ገደብ ተጥሎባቸዋል።

አሌክሳንደር ራኮቭስኪ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች፣ በተለይም ስለ ሰሜኑ ንጉሥ በሚናገሩት ትንቢቶች ላይ ማሰላሰሉ ለመጽናት እንደረዳው ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “በሚያስጨንቁኝ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ስለ ስደት በሚናገሩ ትንቢቶችና በፍጻሜያቸው ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል። በተጨማሪም ይሖዋ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን እንደሚረዳን በገባው ቃል ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል።”

እነዚህ ሦስት ወንድሞች አዎንታዊ አመለካከት ይዘው እንደሚቀጥሉና ጠንካራ እምነታቸው ይህን ፈተና በጽናት ለመቋቋም እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ነን።—ፊልጵስዩስ 1:29