በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከላይ በስተ ግራ፦ የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስትር መጋቢት 15, 2023 የላኩት ደብዳቤ። ከታች፦ ከትምህርት ቤት የተባረሩ የይሖዋ ምሥክር ተማሪዎችና ወላጆቻቸው

ግንቦት 1, 2023
ሩዋንዳ

የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስትር የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ መብት የሚያስከብር ውሳኔ አስተላለፈ

የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስትር የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ መብት የሚያስከብር ውሳኔ አስተላለፈ

መጋቢት 15, 2023 የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስትር በመላው ሩዋንዳ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ከትምህርት ገበታቸው የተባረሩ የይሖዋ ምሥክሮችን እንደገና እንዲቀበሉ ትእዛዝ አስተላልፈዋል። ከሕሊናቸው ጋር በሚጋጩ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ ቢያንስ 80 ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ተባርረው ነበር።

የትምህርት ሚንስትሯ በመላው ሩዋንዳ ለሚገኙ ለሁሉም ከንቲባዎችና የትምህርት ቤት አስተዳደሮች በላኩት ደብዳቤ ላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ማፈናቀል እንዲቆም መመሪያ ሰጥተዋል። ሚንስትሯ የሩዋንዳን ሕገ መንግሥት በመጥቀስ እንዲህ ብለዋል፦ “ሁሉም ሩዋንዳዊ የመማር መብት አለው። መንግሥትም የእያንዳንዱን ዜጋ የሐሳብ፣ የሕሊና፣ የሃይማኖትና የአምልኮ ነፃነት እንዲሁም እምነቱን በይፋ የመግለጽ መብት ያስከብራል።” ከዚህም በተጨማሪ አንድን ተማሪ የትምህርት ዕድል የሚነፍግ ማንኛውም ሰው “ከባድ ጥፋት በመፈጸሙ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰድበታል” ብለዋል። ሚንስትሯ በደብዳቤው ላይ ለትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፦ “አንድም ተማሪ በአስተሳሰቡ፣ በሕሊናው፣ በሃይማኖቱ ወይም በአምልኮው ምክንያት ከትምህርት ቤት ሊባረር አይገባም . . . በመሆኑም የትምህርት ቤት አስተዳደሮች እንዲህ ያለውን የአሠራር ግድፈት ሊያስተካክሉና የተባረሩትን ተማሪዎች እንደገና ሊቀበሉ ይገባል።”

ከትምህርት ቤት ከተባረሩት አንዷ እህት ዣኔት ኒዮንኩሩ ናት። እንዲህ ብላለች፦ “ከትምህርት ቤት ከተባረርኩ በኋላ ለአንድ ዓመት ትምህርቴን አቋርጬ ነበር። በኋላ ላይ የሚቀበለኝ ትምህርት ቤት ባገኝም በየቀኑ ለሁለት ሰዓት በእግሬ መጓዝ ነበረብኝ።” ሩቅ ቦታ ወዳሉ ትምህርት ቤቶች መሄድ ያልቻሉት ግን ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገድደዋል።

የወንድም ሃኪዚማና ሦስት ልጆች፣ ትምህርት ቤቱ ባዘጋጀው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ተባርረው ነበር። ወንድም ሃኪዚማና እንዲህ ብሏል፦ “ለትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ደብዳቤ የላክን ቢሆንም ምላሽ አልሰጠንም። ከዚያም አልፈን የትምህርት ቤቱን ዳይሬክተር አነጋግረነው ነበር። ልጆቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው አቋማቸውን ሲያስረዱ አዳመጣቸው፤ ሆኖም ችግሩ መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም። ሚንስትሯ ያስተላለፉት መመሪያ አስደስቶናል። መመሪያው ከተላለፈ በኋላ ከከፍተኛ አስተዳዳሪዎቹ ጋር ተገናኝተን የተነጋገርን ሲሆን ልጆቻችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸዋል።”

የትምህርት ሚኒስትሯ በሩዋንዳ ያሉ የይሖዋ ምሥክር ተማሪዎች መብት እንዲከበር መመሪያ በማስተላለፋቸው አመስጋኞች ነን። እነዚህ ተማሪዎች “ጥሩ ሕሊና” ይዘው መቀጠል ችለዋል፤ እንዲሁም የይሖዋን ስም አስከብረዋል።—1 ጴጥሮስ 3:16