ኅዳር 18, 2019
ሰሜን መቄዶንያ
በልዩ የስብከት ዘመቻ ለመካፈል ‘ወደ መቄዶንያ መሻገር’
የሰሜን መቄዶንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ከነሐሴ 1 እስከ ጥቅምት 31, 2019 ድረስ የዘለቀ ልዩ የስብከት ዘመቻ አዘጋጅቶ ነበር፤ ዓላማው በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ ለሚገኙ መቄዶንያኛ እና አልባኒያኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መስበክ ነበር።
በሰሜን መቄዶንያ ከ1.3 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች መቄዶንያኛ ተናጋሪ ሲሆኑ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ አልባኒያኛ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 1,300 አስፋፊዎች መካከል ለመቄዶንያኛ ተናጋሪዎች የሚሰብኩት 1,000 የሚያህሉ አስፋፊዎች ናቸው፤ ለአልባኒያኛ ተናጋሪዎች የሚሰብኩት ደግሞ 20 አስፋፊዎች ብቻ ናቸው። በዘመቻው ወቅት በአካባቢው ያሉ አስፋፊዎችን ለመርዳት ከሰባት አገሮች ማለትም ከስዊድን፣ ከስዊዘርላንድ፣ ከቤልጅየም፣ ከአልባኒያ፣ ከኦስትሪያ፣ ከጀርመንና ከጣሊያን 476 አስፋፊዎች ወደ ሰሜን መቄዶንያ መጥተው ነበር።
በዘመቻው ወቅት አንድ ወንድም ከአንድ የፍየል እረኛ ጋር ተገናኘ። እረኛው፣ እያነጋገረው ያለው ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ሲገነዘብ ቦርሳውን ከፍቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ አወጣ። ከዚያም ይህን መጽሐፍ የሰጡት፣ ከአሥር ዓመት በፊት በተደረገ ልዩ የስብከት ዘመቻ ለመካፈል ከጣሊያን የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ለወንድም ነገረው። በተጨማሪም እረኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በየዕለቱ እንደሚያነብብ እንዲያውም አንዳንዶቹን ምዕራፎች በቃሉ እንደሚያውቃቸው ተናገረ። በመሆኑም ወንድሞች እሱን ተመላልሰው ለመርዳት የሚያስችል ዝግጅት አደረጉለት።
የመቄዶንያኛ እና የአልባኒያኛ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ያደረጉት ታላቅ ድጋፍ፣ ጳውሎስ ‘ወደ መቄዶንያ ተሻግሮ እንዲረዳ’ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመቀበል ያሳየውን ፈቃደኝነት ያስታውሰናል።—የሐዋርያት ሥራ 16:9