በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 3, 2024
ሰርቢያ

ርቀው በሚገኙ የሰርቢያ ክልሎች የተከናወነ ልዩ የስብከት ዘመቻ አስደናቂ ውጤት አስገኘ

ርቀው በሚገኙ የሰርቢያ ክልሎች የተከናወነ ልዩ የስብከት ዘመቻ አስደናቂ ውጤት አስገኘ

ከሰርቢያ እና ከሞንቴኔግሮ የተውጣጡ ከ600 በላይ ወንድሞችና እህቶች፣ ርቀው በሚገኙ የሰርቢያ ክልሎች ከግንቦት 17 እስከ 26, 2024 በተካሄደ ልዩ የስብከት ዘመቻ ላይ ተካፍለዋል። በሰርቢያ የይሖዋ ምሥክሮች በአካል የተካፈሉበት እንዲህ ያለ የስብከት ዘመቻ ሲከናወን ከ20 ዓመታት ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ነው። ከ1.5 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች (ከሰርቢያ ሕዝብ ሩብ ያህል የሚሆነው) የይሖዋ ምሥክሮች አዘውትረው ሊሄዱባቸው በማይችሉ ራቅ ያሉ ክልሎች እንደሚኖሩ ይገመታል። በዚህ ዘመቻ ወቅት ከ1,800 የሚበልጡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላቸው ጠይቀዋል!

ቤሊ ፖቶክ በተባለው ከተማ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ባደረገችው ውይይት የተደሰተች አንዲት ሴት ለጎረቤቶቿ ስልክ እየደወለች እንዲህ አለቻቸው፦ “ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግሯችሁ ሰዎች እየመጡ ነው። በደንብ አዳምጧቸው!” በመንደሩ ውስጥ ባንኳኩት የመጨረሻው ቤት ያገኟት ሴት መምጣታቸውን በጉጉት እየጠበቀች ነበር፤ በደስታ ሰላም ካለቻቸው በኋላ ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ከዚያም በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ ተገኝታ እንደምታውቅ ነገረቻቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ በደስታ ተቀበለች።

ሁለት እህቶች በትርጎቪሽቴ መንደር የሚገኙ አንዲት አረጋዊት ሴትን ሲያነጋግሩ

ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ስሜዴረቭስካ ፓላንካ በተባለው ከተማ ውስጥ የጽሑፍ ጋሪ አጠገብ ቆመው እያለ ራዶሚር የተባለ ሰው ቀረብ ብሎ አነጋገራቸው። በአምላክ የሚያምኑ ሰዎች በሚኖርበት ከተማ ውስጥ በማየቱ ምን ያህል እንደተደሰተ ነገራቸው። ከዚያም በጋሪው ላይ የተለጠፈው “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በነፃ” የሚለው ማስታወቂያ ምን ማለት እንደሆነ ጠየቃቸው። ወንድሞች አሳታፊ ስለሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኮርስ ካብራሩለት በኋላ ራዶሚር እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ በደስታ ተቀበለ።

ይህ ልዩ የስብከት ዘመቻ በሰርቢያ ለሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለተጠሙ ሁሉ ታላቅ በረከት አስገኝቷል።​—ዮሐንስ 7:37