በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ውስጠኛው ምስል በስተ ግራ፦ አንዲት እህት ወደ መረጃ መስጫ ቦታው የሄደን ሰው ስታነጋግር። መካከለኛው ምስል፦ ዓለም አቀፉ የቤልግሬድ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ የተካሄደበት የቤልግሬድ የኤግዚቢሽን ማዕከል

ታኅሣሥ 13, 2023
ሰርቢያ

በዓለም አቀፉ የቤልግሬድ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ምሥራቹን መስበክ

በዓለም አቀፉ የቤልግሬድ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ምሥራቹን መስበክ

ከጥቅምት 21 እስከ 29, 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በቤልግሬድ፣ ሰርቢያ 66ተኛው ዓለም አቀፉ የቤልግሬድ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ተካሂዶ ነበር። ከ190,000 በላይ ሰዎች በአውደ ርዕዩ ላይ ተገኝተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ቃል ስለሚሰጠው ጠቃሚ ምክር ለሰዎች ለማሳወቅ በዚህ አውደ ርዕይ ላይ የመረጃ መስጫ ማዕከል አዘጋጅተው ነበር። ከ100 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለጥያቄዎቻችን መልስ ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለጎብኚዎች አሳይተዋል።

በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት ሴት ወደ መረጃ መስጫ ቦታው በመሄድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዙ ብዙ ጥያቄዎች እንዳሏት ለእህታችን ነገረቻት። ሴትየዋ በመጨረሻ ለጥያቄዎቿ መልስ ሊሰጣት የሚችል ሰው በማግኘቷ በጣም ተደሰተች። እህታችንና ሴትየዋ ውይይታቸውን ለመቀጠል ቀጠሮ ያዙ።

አንድ ወጣት ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የሚል ርዕስ ያለውን ብሮሹር ወሰደ። ወጣቱ በአምላክ ቢያምንም ስለ ፍጥረት የሚገልጸውን ዘገባ ለመረዳት እንደሚቸገር ገለጸ። ለምሳሌ ‘መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ አምላክ ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ቃል በቃል በስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ ያስተምራል?’ የሚል ጥያቄ ነበረው። ወንድሞች ይህንኑ ጥያቄ በቀጥታ የሚመልስ ርዕስ ከ​jw.org ላይ ሲያሳዩት ወጣቱ በጣም ተደሰተ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሁለት ወጣት ሴቶች ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 እና 2 የተባሉት መጻሕፍት ትኩረታቸውን ሳቡት። ወጣቶቹ መጻሕፍቱ እውነተኛ ጓደኞችን ስለማፍራት፣ በትምህርት ቤት ውጤታማ ስለመሆን፣ በወረት ፍቅርና በእውነተኛ ፍቅር መካከል ስላለው ልዩነት እንዲሁም እነዚህን ስለመሳሰሉ ሌሎች አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳዮች እንደሚናገሩ ሲያውቁ በጣም ተደሰቱ። ከሁለቱ ወጣቶች አንዷ “በጣም ደስ የሚሉ መጽሐፎች ናቸው። በእርግጠኝነት እናነብባቸዋለን!” በማለት በደስታ ተናግራለች።

በቤልግሬድ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአውደ ርዕዩ ላይ ላከናወኑት ትጋት የተሞላበት ሥራ እናደንቃቸዋለን። ይሖዋ ‘ስሙን በይፋ ለማወጅ’ ላደረጉት ጥረት እንዲባርካቸው እንመኛለን።—ዕብራውያን 13:15