ጥር 2, 2024
ሱዳን
በሱዳን ያሉ ወንድሞችና እህቶች በጦርነት ምክንያት ድጋሚ ለመሸሽ ተገደዱ
የሱዳን ዋና ከተማ በሆነችው በካርቱም በሁለት ታጣቂ ቡድኖች መካከል ጦርነት ሲካሄድ እንደቆየ ይታወቃል፤ ይህ ግጭት ታኅሣሥ 15, 2023 ላይ ከአገሪቱ ከተሞች መካከል በትልቅነት ሁለተኛዋ ወደሆነችው ወደ ወድ መደኒ ተዛመተ። ቀደም ሲል jw.org ላይ እንደተገለጸው ሚያዝያ 2023 ላይ ጦርነቱ በካርቱም ሲቀሰቀስ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ከዋና ከተማዋ በስተ ደቡብ ምሥራቅ 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወድ መደኒ ሸሽተው ነበር። አሁን ከእነዚህ ወንድሞችና እህቶች መካከል ከ150 የሚበልጡት ከጦርነቱ ለማምለጥ ሲሉ ድጋሚ ለመሸሽ ተገደዋል።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን መካከል ጉዳት የደረሰበት ወይም የሞተ የለም
ቢያንስ 158 የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ተፈናቅለዋል። አንዳንዶቹ ከነበሩበት አካባቢ ሸሽተው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ከተሞች ወይም አገሮች በሰላም ደርሰዋል
10 ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ጥቂት ዘመዶቻቸው አሁንም በወድ መደኒ ይገኛሉ
የእርዳታ እንቅስቃሴ
የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና በአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎች በአደጋው ለተጎዱት መንፈሳዊ ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ
በሱዳን እና በአጎራባች አገሮች ያሉ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች የእርዳታ ሥራውን ማስተባበራቸውን እንዲሁም ምግብ፣ መድኃኒትና መጠለያ የመሳሰሉ ቁሳዊ ድጋፎችን መስጠታቸውን ቀጥለዋል
የሚገርመው በወድ መደኒ ጦርነቱ ከመጀመሩ ልክ ከአንድ ሳምንት በፊት የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ የተፈናቀሉት ወንድሞችና እህቶች “በትዕግሥት ጠብቁ”! የሚል ርዕስ ያለውን የ2023 የክልል ስብሰባ ፕሮግራም ቅጂ በአረብኛ እንዲመለከቱ ዝግጅት አድርጎ ነበር። በስብሰባው ላይ ከተገኙት ወደ 200 የሚጠጉ ተሰብሳቢዎች መካከል በጦርነቱ ምክንያት ከካርቱም ተፈናቅለው የመጡ 145 ወንድሞችና እህቶች ይገኙበታል። በክልል ስብሰባው ላይ ከተገኙት መካከል ብዙዎቹ ወቅታዊ ለሆነው መንፈሳዊ ምግብ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በተለይ ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ስላጋጠማቸው ሰዎች በሚያሳየው “መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ” በተባለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማ በጣም ተበረታተዋል። በዚህ የክልል ስብሰባ ላይ ሰባት ሰዎች ተጠምቀዋል።
በሱዳን ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በጽናት መጋፈጣቸውን እንዲቀጥሉ እንጸልያለን፤ ደግሞም ይሖዋ ‘ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ የሚያስወግድበትን’ ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።—መዝሙር 46:9