በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሴራ ሊዮን የሚኖር አንድ ቤተሰብ አባላት ንግግሩን በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ከተመለከቱ በኋላ አዲሱን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ይዘው

ግንቦት 4, 2020
ሴራ ሊዮን

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በክሪዮ ቋንቋ ወጣ

ፕሮግራሙ ሴራ ሊዮን ውስጥ በብሔራዊ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተሰራጭቷል

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በክሪዮ ቋንቋ ወጣ

በሴራ ሊዮን ክሪዮ ቋንቋ መስክ የሚያገለግሉት ከ2,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ሚያዝያ 26, 2020 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በክሪዮ ቋንቋ በመውጣቱ በጣም ተደስተዋል።

መንግሥት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ባወጣቸው ገደቦች የተነሳ ወንድሞቻችን ለዚህ ልዩ ፕሮግራም አንድ ላይ መሰብሰብ አልቻሉም። ይህን ልዩ ፕሮግራም በኢንተርኔት ማሰራጨትም አልተቻለም፤ ምክንያቱም በሴራ ሊዮን ያሉት አብዛኞቹ አስፋፊዎች በተለይም በትናንሽ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ የላቸውም።

የላይቤሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አልፍሬድ ጋን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በክሪዮ ቋንቋ መውጣቱን ሲያበስር

በመሆኑም በሴራ ሊዮን የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት የሚከታተለው የላይቤሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን የሚገልጽ አጠር ያለ ንግግር ለመቅረጽ ከበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ ፈቃድ አገኘ። ከዚያም አስፋፊዎች ይህን ልዩ ፕሮግራም በሬዲዮ ወይም በቴሌቪዥን እንዲከታተሉ ተነገራቸው፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሱ እንደሚወጣ አልተነገራቸውም።

መጽሐፍ ቅዱሱ እንደወጣ ከመገለጹ ከጥቂት ቀናት በፊት አዲሶቹን መጽሐፍ ቅዱሶች የያዘ የታሸገ ፖስታ በየአስፋፊዎቹ ቤት ተላከላቸው። እሽጉ ላይ ከልዩ ፕሮግራሙ በፊት ፖስታውን እንዳይከፍቱት የሚገልጽ መመሪያ ነበር።

ከሌላ አገር ወደ ሴራ ሊዮን መጥታ የምታገለግለው እህት ሜጋን ዲያዝ መጽሐፍ ቅዱሱ እንደወጣ እንዲህ ብላለች፦ “ጥናቴ ስልክ ደውላ ንግግሩን እንዳዳመጠችና ይሖዋ ይህን አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሰጠን በጣም እንደተደሰተች ነገረችኝ። ነገ የምናጠናው አዲሱን መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ነው።”

ክሪዮ ተናጋሪ የሆነ ቶውንካራ የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲህ ብሏል፦ “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በክሪዮ ቋንቋ መውጣቱ ይሖዋ መልእክቱ ለሁሉም ሰው እንዲደርስ እንደሚፈልግ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው፤ ሰዎቹ ራሳቸው እንዲማሩ ብቻ ሳይሆን መልእክቱን በደንብ ተረድተውት ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩትም ይፈልጋል። ይህን አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋችን በማግኘታችን በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ!”

ክሪዮ ከእንግሊዝኛ የተወረሰ ቋንቋ ሲሆን ሴራ ሊዮን ውስጥ በስፋት ይነገራል። አራት ተርጓሚዎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ክሪዮ ተርጉመው ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ተኩል ፈጅቶባቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱሱ የኤሌክትሮኒክ ቅጂ ሰኞ ሚያዝያ 27 jw.org ላይ ወጥቷል።

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በክሪዮ ቋንቋ በመውጣቱ በሴራ ሊዮን ከሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ተደስተናል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰማዩ አባታችን ከይሖዋ ያገኘነው ተጨማሪ ‘መልካም ስጦታና ፍጹም ገጸ በረከት’ ነው።—ያዕቆብ 1:17