ጥር 31, 2023
ሴኔጋል
በሴኔጋል በተካሄደ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ የJW.ORG ኪዮስክ የጎብኚዎችን ትኩረት ሳበ
ከታኅሣሥ 15 እስከ 31, 2022 ሴኔጋል ውስጥ ዓመታዊው የዳካር ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ተካሂዶ ነበር፤ የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ተሳትፈዋል። አውደ ርዕዩ መታየት ከጀመረ 30 ዓመት አስቆጥሯል። የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ሕዝባዊ አገልግሎቶችና ባሕላዊ ፕሮግራሞች ለእይታ የሚቀርቡበት መድረክ ነው። በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና ከዓለም ዙሪያ መቶ ሺዎች ታድመዋል።
ወንድሞችና እህቶች፣ jw.org ላይ የወጡ ነገሮች እንዲሁም ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚገልጹ ጽሑፎች ለእይታ የሚቀርቡበት የመረጃ ኪዮስክ ከፍተው ነበር። አስፋፊዎች የይሖዋ ወዳጅ ሁን እና የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽኖች በሚሉት ዓምዶች ሥር ያሉትን ቪዲዮዎች አሳይተዋል፤ እኩዮችህ ምን ይላሉ? በሚለው ዓምድ ሥር ያሉ የወጣቶች ቃለ መጠይቆችም ለእይታ ቀርበዋል።
ስለ ድረ ገጻችን የማያውቁ በርካታ ጎብኚዎች እዚያው ኪዮስኩ አጠገብ በስልካቸው ድረ ገጹን መጎብኘት ችለዋል። jw.org የአገሬውን የዎሎፍ ቋንቋን ጨምሮ ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች እንደሚገኝ ሲያውቁ ብዙዎች ተገርመዋል። ጎብኚዎቹ ባቀረቡት ጥያቄ ከ3,000 የሚበልጡ ጽሑፎች ተበርክተዋል።
አንድ ጎብኚ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፦ “ከአጠቃላዩ አውደ ርዕይ በጣም የተጠቀምነው የእናንተ ኪዮስክ ጋር ባሳለፍነው ጊዜ ነው።” ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ምርጥ ኪዮስክ በሚል ሽልማት ቢኖር ኖሮ የምታሸንፉት እናንተ ናችሁ!” ብሏል።
ሥራውን በማስተባበር ያገዘው ወንድም ማርቲን ሎውድ እንዲህ ብሏል፦ “ከተለያዩ አገራት የመጡ ጎብኚዎች ማግኘታችን አስደስቶናል። ብዙዎች፣ በነፃ ለምንሰጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ ልባዊ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።”
በዚህ ፕሮግራም ላይ በተገኘው የሚያበረታታ ውጤት ተደስተናል። የይሖዋ ሕዝቦች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን “ጥበብ” ለብዙዎች ከሚያሰሙባቸው በርካታ መንገዶች ይህ አንዱ ብቻ ነው።—ምሳሌ 3:21, 22